ዛሬ የከተማ አስተዳደራችን የ90 ቀናት የመንግስት እና የፓርቲ ስራዎች ዕቅድ ላይ ከመላው የከተማችን አመራሮች ጋር ተወያይተን ወደ ተግባር አስገብተናል።
በድህረ ምርጫ በፍጥነት ፈታችንን ወደ ሥራ በመመለስ ፈጣን ውጤቶችን ማስመዝገብ፣ ተከታታይና አዳዲስ ነገሮችን መተግበር፣ ህብረተሰባችን ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በላቀ ትጋትና ያለ እረፍት መፈጸም የሚያስችል እቅድ ይዘን በልዩ ትኩረት የምንፈፅም ይሆናል።
ከሰኔ 9 እስከ ጳጉሜ 5 በሚቆየው 90 ቀናት ውስጥ የምንፈፅማቸው ዋና ዋና ግቦች፤ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ አገልግሎት የማሻሻል ስራን በማጠናከር የመሶብ አንድ ማእከል ዲጂታል አገልግሎትን ማስፋት፣ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ፣ የንግድ ስርዓቱን መግራት፣ የስራ እድል ፈጠራ እና የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት ላይ መስራት፣ በአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ የከተማ ግብርና እና የሌማት ትሩፋት፣ የሰላም ግንባታ ስራዎች፣ የገቢ አሰባሰብ፣ ልመናንና ተረጂነትን መቀነስ፣ የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብርን በተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎ መተግበር፣ የኢትዮዽያ ታምርት ንቅናቄን በአዲስ ቅኝት መምራት፣ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን በጥራት እና በተያዘላቸው የጊዜና በጀት ገደብ ማጠናቀቅ፣ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ማጠናከር … ወዘተ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈፀም ተዘጋጅተናል።
የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ዝግጅት ላይ በትኩረት በመስራት አዲሱ በጀት ዓመት ህዝባችንን ይበልጥ የምናገለግልበት፣ አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ጉዟችንን የምናረጋግጥበት እንዲሆን ከእቅድ ዝግጅት እስከ ተግባር አፈፃፀም በጠንካራ ክትትልና ድጋፍ የምንፈፅም ይሆናል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.