የመረጠንን ህዝብ የምናመሰግነው በቃላት ብቻ ሳይሆን ችግሩን የሚፈቱ ተጨባጭ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት ነው።
በተጣለብን በህዝብ እምነት ዳግም ኢትዮጵያን ለመምራት ተጨማሪ አምስት ዓመት ለፓርቲያችን ብልፅግና በተሰጠበት ማግስት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት እጅግ የተጎሳቀለውን፥ ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ መኖሪያ ቤቶችንና አካባቢውን ወደ ንፁህ ፥ውብ መንደር ለመቀየር ከከንቲባ ፅ/ቤት ጀርባ ላይ “ አራዳ የበጎነት መንደር “ግንባታን ጀምረናል።
በክረምት በጐ ፍቃድ 2500 ቤቶችን ለመገንባት ያቀድን ሲሆን ፣ዛሬ ባስጀመርነዉ የአራዳ የበጎነት መንደር ባለ 9 ወለል 8 ህንፃዎች እና ሁለት በላ 4 ወለል የገበያ ማዕከል ያሉት ሲሆን ፥ የተጎሳቆሉ ቤቶችን እና አካባቢውን በመቀየር ለኑሮ ምቹ የሆኑ ፣ ንጽሕናቸውን የጠበቁ የመኖሪያ ቤቶችና አካባቢዎች፣ የጋራ መገልገያዎችን እና አረንጓዴ ሥፍራዎችን እንዲሁም ህፃናት ቦርቀው የሚጫወቱባቸው የስፓርት ሜዳዎች በጥቅሉ ለሰው ልጆች ምቹና ክብር የሚመጥን ዘመናዊ አኗኗርን የሚፈጥር የከተማዋን ውበት የሚቀይር መንደር ነው።
በክረምት በጎ ፍቃድ የምንገነባው ቤት ብቻ ሳሆን አካባቢን እናፀዳለን፥ የጐርፍ መከላከያዎች እንገነባለን፣ ምንም ገቢ ለሌላቸው ማዕድ እናጋራለን፥ ደም ልገሳ እናካሄዳለን፥ የጀመርነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ እንተክላለን፣ የማጠናከርያ ትምህርት እንሰጣለን፣ የነፃ ህክምና አገልግሎት ፣ የመንገድ ትራፊክ ማሳለጥ እንዲሁም ከተማችን ውብ ፥ ለኑሮ ምቹ ከተማ የማድረግ ስራችን እጠናክረን እንሰራለን።
የምንገነባው መተማመንን፣ ፅናትን፣ አብሮነትን፣ ወንድማማችነትን/ እህትማማችነትን፣ ክብራችንን በጥቅሉ የኢትዮዽያን የብልፅግና መንገድ ነው።
የከተማችን ባለሃብቶች የህዝባችን አኗኗር ለመቀየር በምንሰራቸው ልማቶች ሁሉ ስንጠራችሁ ቀና እና ፈጣን ምላሽ ስለምትሰጡን እጅግ አድርገን እያመሰገንን፤ ዛሬም ግንባታውን የጀመርነው የአራዳ የበጎነት መንደር አብራችሁ ለመገንባት ቃል የገባችሁ ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፥ የኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣በላይነህ ክንዴ ፥ ያደታ ጁነዲን እያንዳንዳቸው አንድ ባለ 9 ወለል ህንፃ የሚገነቡ ሲሆን እንዲሁም ቲኤንቲ ኮንስትራክሽን፣ ግራንድ ሌጋሲ ሃውስ፥ ኢቲ ኦንላይን ኮሌጅ፣ አብይ ማስረሻ፥ ዴማ ሪልስቴት ፥ ቴምር ሪልስቴት፥ ስናፕ ትሬዲንግ፥ ጊፍት ሪልስቴት፥ መሃመድ አድናን ፥ አሚር በድሩ በጋራ ለመገንባት አብራችሁን ስለሆናችሁ በነዋሪዎች እና በራሴ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.