Ethiopia Delivers From Reform...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

Ethiopia Delivers From Reform Lasting Change

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዲጂታል አማካሪ የሆኑት ሚሪያም ሰዒድ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ተበታትነው የነበሩ አሠራሮችን በዲጂታል ማንነት፣ በክፍያ እና በዳታ ልውውጥ የተቀናጁ የኢኮኖሚ መዋቅሮች ውስጥ በማስገባት፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን በማገናኘት እንዲሁም የሃገር በቀል አቅምን በጋራ በማሳደግ፣ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ምቹ የሆነ የኢኮኖሚ መሠረት እየጣለችና ይሄንኑ ሪፎርም ወደ ምርታማነት እየቀየረች እንደምትገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገር ውስጥ መረጋጋትንና ተዓማኒነትን መልሶ ማምጣቱን ገልጸው፤ ይህም የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ገበያውን ነፃ በማድረግ፣ የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲን በማዘመን፣ እንዲሁም ለዘላቂና አካታች ዕድገት ጠንካራ መሠረት ለመጣል የፋይናንስ ዘርፉን በማጠናከር የተገኘ መሆኑን አብራርተዋል።

‎ በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ትዕግሥት ፍስሀ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ አዲስ የከተማ ልማት ምዕራፍ ውስጥ እየገባች ሲሆን፥ ትኩረቱም ከተሞችን ማሰፋፋት ላይ ብቻ ሳይሆን ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንዲሁም ምቹ፣ ተወዳዳሪ፣ ሁሉን አቀፍና ዘመናዊ ከተሞች ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለጋራ ብልፅግና ቀጣይ ሞተር እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

 

የግብርና ትራንስፎሜሽን ኢንስትቲዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ  ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ፣ የግብርና ዘርፍ የለውጥ ጉዞን በተመለከተው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ስልታዊ ኢንቨስትመንቶችን እና ጉልህ ማሻሻያዎችን በማከናውን የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ ከነበረበት ከእጅ ወደ አፍ ልምምድ ተላቃ አሁን ላይ ከእርሻ ወደ ንግድ ብሎም የሉዓላዊነት መሰረት የተሸጋገረ መሆኑን አመላክተዋል፤ 

‎ለዚህም ከ10 ዓመቱ መሪ እቅድ ጋር የተጣጣሙ ስትራቴጂዎችንና የፖሊሲ ለውጦ ማዕቀፎችን በመንደፍ፤ የመንግሥት፣ የግል ዘርፉንና የህዝብ አጋርነትን በማጠናከር፣ ፈጠራንና የግብርና ቢዝነስን በማስፋፋት እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን በማሳደግ የግብርናው ዘርፍ ይበልጥ ምርታማ፣ በገበያ ላይ የተመሰረተ እና ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ቀውሶችን የመቋቋም አቅሙ የዳበረ እንደሆነ ገልጸዋል። ቀደም ሲል ከውጪ በሚገቡ ምርቶች ላይ በስፋት ተመርኩዛ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ተተኪ ምርቶችን በማሳደግ፣ የሌማት ትሩፋትና መሰል ሀገር በቀል ተነሳሽነቶችን በማዳበር፣ ቴክኖሎጂንና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመታገዝ  ለወጣቱ የስራ እድልን ከመፍጠር ባሻገር ሀገሪቱ በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጉዞ አመርቂ ውጤት እያስገኘ ይገኛል፤ እነዚህ የታቀዱና መጻኢውን ጊዜ ያገናዘቡ ስልታዊ እርምጃዎች ለዘላቂ የግብርና አብዮት፣ ለገጠር ብልጽግና እና ለጠንካራ ኢኮኖሚ መሰረት እየጣሉ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ወደፊት እየተራመደችና ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኑን በተግባር ያሳያሉ።

‎በማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ኢንጂነር ሐና ብርሃኑ፣ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ከነበረበት ደካማ አፈጻጸም ተነስቶ አሁን ላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ስትራቴጂካዊ ምሰሶዎች አንዱ መሆን የቻለበትን የማዕድን ትራንስፎርሜሽን ጉዞ አቅርበዋል።

‎ በቁርጠኛ ማሻሻያዎች፣ በገበያ መልሶ ማዋቀር እና እሴትን መጨመር በሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶች በመታገዝ ዘርፉ ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢን እያስገኘ፣ የገቢ ምርቶችን ጥገኝነት እየቀነሰ እና ለኢንዱስትሪ ልማት አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ኢንጂነር ሐና አመላክተዋል።

‎በወርቅ፣ በወሳኝ ማዕድናት፣ በነዳጅ እና በማዳበሪያ ምርት ላይ እየተስፋፋ በመጣው የኢንቨስትመንት ለውጦች፣ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት አቅም ወደ ተጨባጭ ብሔራዊ ዕድገት እየቀየረችው ትገኛለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ እነዚህ ስኬቶችም በሀገር በቀል ቅኝት የሪፎርም ማሻሻያ፣ በገዘፈ ርዕይ እና አፈጻጸም ድምር ውጤት እንደሚያስገኙ ህያው ማረጋገጫዎች ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ብሩክ ታዬ በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት ጉዞ ለዘመናት ከዘለቀው ሀገራዊ ትልም ተነሥቶ አሁን ላይ በትጉህና ግልጽ መርሆዎች እንዲሁም በተዋቀረ አፈጻጸም ወደሚመራ የለውጥ ዘመን ተሸጋግሯል፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ የለውጡ መንግሥት ሀገራዊ ተስፋን ከተቋማዊ አቅም ጋር ወደሚያጣጥም፣ ይበልጥ አመቺ፣ ቅደም ተከተላዊ እና የፋይናንስ ሥነ-ሥርዓትን ወደ ተከተለ አካሄድ ቁርጠኛ ሽግግር ያደረገ ሲሆን ይህም መሠረተ ልማትን ወደ ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ እሴት እና ለትውልድ ተሻጋሪ ሀብት እንዲቀየር እያደረገው ይገኛል።

 

‎ የንጹሕ ኢነርጂ፣ የዲጂታል ማስፋፊያ፣ የትራንስፖርት፣ የኮንስትራክሽን እና የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ሀገሪቱ የምታደርገውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ እየመሩት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ዕድገቷ ራሱን ችሎ የሚቀጥልና ለውጥ የሚያመጣበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በትጋት እየገነባች ትገኛለች!

 

#PMOEthiopia #EthiopiaDelivers

 

 


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.