የእንጦጦ - ቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የዚህ ትውልድ ደማቅ አሻራ፤ የመጪው ትውልድ የልማት ምንዳ!!
በአሻጋሪ እሳቤ፣ የጋራ ህልምን ወደ ታላቅ ድል መቀየር እንደሚቻል አዲስ አበባ በተግባር እያሳየች ትገኛለች። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ እና በክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚመራው፣ «ሰርቶ ማሳየትና ሰርቶ ማሰራት»ን መርሁ ያደረገው ቁርጠኛ አመራር ለከተማችን ዘላቂ ትንሳኤ የማይደበዝዝ ታሪካዊ አሻራውን አሳርፏል።
የዚህ ታላቅ ስኬት ማሳያ የሆነውና በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት የተደረገው የእንጦጦ _ ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት የአዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻነት በማሳደግ ረገድ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
በዛሬው ዕለት የሀገራችን ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ስመ ጥር አርቲስቶችና የብሔራዊ ጥበባት ማህበራት ፕሬዚዳንቶች የእንጦጦ _ ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት በመጎብኘት፣ በጥበብና በልማት መጋመድ ዙሪያ ተጨማሪ ተሞክሮና መነሳሳትን ቀስመዋል።
10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት የያዘው ይህ ፕሮጀክት፣ በአጠቃላይ 87 ነጥብ 6 ሄክታር መሬትን በአረንጓዴ ልማትና በዘመናዊ መሰረተ ልማት ያደሰ ታላቅ ክስተት ነው።
ቀደም ሲል በከፍተኛ ብክለት፣ በጎርፍና በአፈር መንሸራተት አደጋ እንዲሁም በፀጥታ ስጋቶች ሳቢያ የአካባቢው ነዋሪዎች ይኖሩበት የነበረውን አስቸጋሪ ህይወት ፕሮጀክቱ ቀይሮታል።
ከተፈጥሮ ጋር በተስማማ እና በዘላቂ ልማት እሳቤ የተገነባው ፕሮጀክቱ በውስጡ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴና ለእግር ጉዞ የሚሆኑ ውብ መንገዶችና ደረጃቸውን የጠበቁ ድልድዮች፣ ዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍት፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ሰፋፊ ፕላዛዎችና የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) እና ንፁህ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ መለስተኛ ግድቦች፣ ሰው ሰራሽ ፏፏቴዎች፣ በርካታ የንግድ ሱቆች እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ (የከተማ ግብርናን የሚያበረታቱ) እፅዋት የተካተቱበት ሰፊ የአረንጓዴ ስፍራዎች የያዘ ነው፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት የልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳርዳር ብርሀኑ ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች በሰጡት ማብራሪያ እንዳመለከቱት፤ ለረጅም ዘመናት ትኩረት ተነፍጎት ለብክለትና ለህገ-ወጥ ግንባታዎች ተጋልጦ የነበረው የቀበና ወንዝ አካባቢ ዛሬ በተባበሩ እጆችና በተደመሩ አቅሞች ማራኪና ሳቢ ገጽታን መላበስ ችሏል ብለዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.