ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያና ምላሽ ይሰጣሉ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ ማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም የመንግሥትን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባሉ።
ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ 17 እና በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 81 ንዑስ አንቀፅ 1 እና 3 መሠረት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ሌሎች የፌዴራሉ መንግሥት ባለሥልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈፃሚውን አካል አሠራር የመመርመር፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን አለው።
በዚሁ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌና የምክር ቤቱ ደንብ መሠረት፤ 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ በሚያካሂደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ በአካል ተገኝተው የመንግሥትን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዓመታዊ በጀት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ የሚሰጡ ይሆናል።
በተያያዘም ምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ የበጀት አዋጁን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የሚገኙ ሲሆን፤ የጉባኤው ሙሉ ሂደትም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ በቀጥታ ሥርጭት ለሕዝብ የሚተላለፍ ይሆናል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.