ኢትዮጵያ እየመከረች ነው !
ኢጋድ ዋና ፀሐፊ ክቡር ወርቅነህ ገበየሁ በሀገራዊ ምክክር መክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓለም ታሪክ ውስጥ በግጭት የተገነባ ወይም ያተረፈ ሀገር አለመኖሩን አስገንዝበዋል። አክለውም በፖለቲካ ባህል ውስጥ ልዩነቶች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ ቢሆንም፤ ትልቁና መሰረታዊው ስህተት ግን እነዚህን ልዩነቶች በኃይል ለመፍታት መሞከር እንደሆነ ነው ያነሱት። ከሁሉ በላይ ልዩነቶችን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ፣ በመነጋገርና በተለያዩ ሰላማዊ መድረኮች መሆኑን ያብራሩት ዋና ፀሐፊው፤ ኢትዮጵያም ለዚህ የሚሆኑ በርካታ ባህላዊ የምክክር መንገዶች ያሏት ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ክቡር ቺፍ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በሀገራዊ ምክክር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የህዝቦቿን ብዝሃነትና ታታሪነት በመጥቀስ ይህ ህዝብ የሰነቀውን ብሩህ ተስፋ ለማሳካት ደግሞ አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ስኬት ቁልፍ መሆኑን አብራርተዋል።
የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ የሰላም እና የደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር ክቡር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ ዛሬ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ትልቅ ተስፋን ሰንቆ በይፋ በተጀመረው ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር መድረክ ላይ በመገኘት የደስታና የጽኑ አጋርነት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።ኮሚሽነሩ በዚህ ታሪካዊ ስፍራ ተገኝተው የዚህ ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ አካል መሆን ለአፍሪካ ህብረት ትልቅ ኩራት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ የሂደቱንም ታላቅነት፣ ስፋትና ጥንካሬ በከፍተኛ ሁኔታ አድንቀዋል። አክለውም የአፍሪካ ህብረት ይህንን ታሪካዊ ክስተት በሙሉ አቅሙ እንደሚደግፍ በማረጋገጥ፣ ይህ የጋራ ጉዞ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን፣ ልማትንና አዎንታዊ ለውጥን ማምጣት እንደምትችል የሚያሳይ ህያው ምስክር መሆኑን በንግግራቸው አመላክተዋል።
በታሪካችን እጅግ ታሪካዊ የሆነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተወካዮች በተገኙበት በከተማችን በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከፍቷል።
በምክክር የምትፀና ሀገር!
ኢትዮጵያ ሀገሬ ይሳካልሽ !
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.