በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነዳጅ ማደያዎች...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነዳጅ ማደያዎች ላይ በተከናወነው የአመታዊ ነዳጅ ሜትር ልኬት ምርመራ ችግር በታየባቸው 91 ነዳጅ ማደያዎች ላይ ተገቢውን የሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አሳውቀ።

ነዳጅ እስትራቴክ ምርት እንደመሆኑ መጠን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቅርቦት፣ ክምችትና ስርጭት አለም ዓቀፍ ደረጃውን በጠበቀ አግባብ ቁጥጥሩን መምራት አስፈላጊ በመሆኑ ከአስመጪ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ተጠቃሚው ህብረተሰብ ድረስ ግብይቱን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊ፣ ተደራሽ እና ከብልሹ አሰራር የፀዳ ለማድረግ የተጠያቂነት ስርዓት በመዘርጋት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
 
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በዘርፉ የሚታየውን ያልተገባ ጥቅም ፈላጊነት በህግና በስርዓት በመምራትና የተጠያቂነት ስርዓትን በመዘርጋት ህብረተሰቡ ለከፈለው ዋጋ ተመጣጣኝ ምርትና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ የነዳጅ ማደያዎችን ሜትር አመታዊ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በመሆኑም በ133 ነዳጅ ማደያዎች በተደረገ የሜትር ምርመራ የመቅጃ ኖዝሎች የልኬት ችግር በታየባቸው 91 ነዳጅ ማደያዎች ላይ በነዳጅ ውጤቶች ግብይት አዋጅ 1363/2017 አንቀፅ 23 እና 25 መሰረት እርምጃ ተወስዷል፡፡

በዚህ መሰረት 3 ነዳጅ ማደያዎች ከ20 ሊትር ስታንዳርድ ከ1 ሊትር እስከ 1 ሊትር ከ560 ሚሊ ሊትር አጉድለው በመሸጥ ሸማቹን ህብረተሰብ ሲያጭበረብሩ በመገኘታቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው ተደርጓል፡፡

በሱፐርቪዥን ጥፋት የተገኘባቸው 3 የነዳጅ ማደያዎች ደግሞ ከአንድ ወር እስከ 2 ወር ለሚሆን ጊዜ ምንም አይነት የነዳጅ ምርት እንዳይደርሳቸውና ከትስስር እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

ከ20 ሊትር ስታንዳርድ ከ500 ሚሊ ሊትር እስከ 999 ሚሊ ሊትር ድረስ በማጉድል ህብረተሰቡን ሲጎዱ የነበሩ 21 የነዳጅ ማደያዎች ላይ የመጨረሻ የፁሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከ20 ሊትር ስታንዳርድ ከ200 ሚሊ ሊትር እስከ 499 ሚሊ ሊትር ድረስ በማጉደል 64 የነዳጅ ማደያዎች ላይ የፁሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በአጠቃላይ በከተማችን ካሉት 133 ነዳጅ ማደያዎች ውስጥ 91 የነዳጅ ማደያዎች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡
 
በቀጣይም በአዋጅ ቁጥር 1363/2017 መሰረት አንቀፅ 25 ንዑስ አንቀፅ 4 መሰረት የነዳጅ መቅጃ መሳሪያዎች የልኬት ሜትር ማስተካከያ ተደርጎበት በፕሎምፕ የታሰረውን የቆረጠ ወይም ልኬቱን ያዛባ ማንኛውም ሰው ከሶስት አመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር ሶስት መቶ ሀምሳ ሺህ እስከ አምስት መቶ ሺህ በሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣ መሆኑን እያሳወቅን ይህ የህግ ማስከበር ስራ ከህብረተሰቡ በሚቀርቡ ጥቆማዎች፣ በድንገተኛ ፍተሻ እና በመደበኛ የልኬት መሳሪያዎች ቁጥጥር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እንገልፃለን፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.