በከተማዋ የፍጆታ አቅርቦትን በማሳደግና ሕገ-ወጥ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በከተማዋ የፍጆታ አቅርቦትን በማሳደግና ሕገ-ወጥ ንግድን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን መከላከል ተችሏል- አቶ ጃንጥራር አባይ

በከተማዋ የተጀመረው የገበያ ማረጋጋት እና የሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ሥራዎች የፍጆታ አቅርቦትን በማሳደግና የኑሮ ውድነትን ትርጉም ባለው መንገድ በመከላከል ረገድ ስኬታማ ውጤት ማስመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ አስታወቁ።

የአዲስ አበባ የገበያ ማረጋጋት፣ ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር እና የ”አዲስ አበባ ታምርት” ግብረ-ኃይል ባለፉት ሁለት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት ገምግሟል፡፡

ግብረ-ኃይሉ በከተማዋ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ከሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሶስት ወራት ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ ባለፉት 60 ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት መድረክ ገምግሟል።

በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ በከተማዋ የፍጆታ አቅርቦትን ማሳደግ እና ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን መከላከል በመቻሉ ገበያውን ማረጋጋት እና የኑሮ ውድነትን ትርጉም ባለው መንገድ መከላከል ተችሏል ብለዋል። 

ባለፉት ሁለት ወራት ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን በማስፈን ረገድ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውንም  ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው አያይዘውም የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት በኩል የነዋሪውን እርካታ ማሳደግ ያስቻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፣ አሁንም ገበያውን በዘላቂነት ለማረጋጋት ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በየደረጃው የሚገኙ የግብረ-ኃይሉ አባላት በጥብቅ ዲሲፕሊን ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የግብረ-ኃይሉ ምክትል ሰብሳቢ እና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከአቅርቦት አንፃር አመርቂ ውጤት የተመዘገበ መሆኑን ገልጸው፣ ክፍተት በሚታይባቸው መስኮች ላይ በቅንጅት ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የግብረ-ኃይሉ ጸሐፊ እና የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመከላከል የግብይት ሂደቱን ፍትሃዊነት በማረጋገጥ ረገድ የተሠራው ሥራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
AMN


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.