ኢትዮጵያ የዘመናት ስብራቶቿን ለመጠገን እየመከረ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ኢትዮጵያ የዘመናት ስብራቶቿን ለመጠገን እየመከረች ነዉ!

የአንዲት ሀገር የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ጉዞ አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው በህዝቦች የጋራ መግባባትና በጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ላይ ሲገነባ ብቻ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ በገለልተኛ ተቋም የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር የቆዩና የተወሳሰቡ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልዩነቶቻችንን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ፈትተን፣ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን የተከፈተ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነዉ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገልተኛ ሆነ ከተመሰረተ ጀምሮ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። አሁን ላይ ሂደቱ እጅግ ተስፋ ሰጪና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ኮሚሽኑ በመላው ሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መዋቅሩን ዘርግቶ፣ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግብዓቶችንና አንገብጋቢ ሀገራዊ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራን በስኬት አጠናቋል።
 
አሁን ላይ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ከ4,000 በላይ ተወያዮቹ ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ከትጥቅ ትግል ወደ ሳላም አማራጭ የተመለሱ ሃይሎች ፣ የዲያስፖራ አባለት፣ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገናኝተው ታሪካዊ ምክክሩን እያሳለጡ  ነዉ። 

ሀገራዊ ምክክር የጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ የወደፊት እጣ-ፈንታ የሚወሰንበት ብሄራዊ መድረክ ነው። ሀገራዊ ምክክርን በአግባቡ በመጠቀም ከተወሳሰበ ቀውስና ከእርስ በርስ ጦርነት ወጥተው ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት የተሻገሩ በርካታ ሀገራትን ማንሳት ይቻላል።

ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት ካደረሰባት ጥልቅ ማህበራዊ ቁስልና የርስ በርስ ጦርነት ስጋት የወጣችው በሀገራዊ ምክክር (CODESA) አማካኝነት ነው። የፖለቲካ ሃይሎች በጥላቻ ፈንታ ይቅርታንና እርቅን በማስቀደማቸው ዛሬ ደቡብ አፍሪካ ጠንካራ ዲሞክራሲ መገንባት ችላለች።

ቱኒዚያ እ.ኤ.አ በ2011 ከነበረው ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ፣ የሀገር መፍረስ ስጋትና አለመረጋጋት ህዝቧን የታደገችው በሲቪል ማህበራት መሪነት በተደረገ ብሄራዊ ምክክር ነው። ይህ ምክክር ሀገሪቱን አዲስና ሁሉን አቀፍ ህገ-መንግስት ለማርቀቅ አብቅቷታል። 

የእነዚህ ሀገራት ተሞክሮዎች የሚያሳየን በቅንነትና በቁርጠኝነት በጠረጴዛ ዙሪያ ከተቀመጥን የማይፈታ የትኛውም ውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ እንደሌለ ነዉ።

ስለዚህ የኢትዮጵያና ህዝቦቿን ሁለንተናዊ ብልፅግና ከልቡ የሚሻ ሁሉ ዜጋ ሀገራዊ ምክክሩ የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የሚወስን ስለሆነ በሃሳብ፣ በዕውቀት፣ በንቁ ተሳትፎና በጸሎት መደገፍ የሁላችንም የዜግነት ግዴታ ነው።

prosperity


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.