ለአዲስ ዓመት በቂ የበዓል የፍጆታ ምርቶች በተ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ለአዲስ ዓመት በቂ የበዓል የፍጆታ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑ ተገለጸ

የአዲስ አበባ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት፣ መስቀልና ኢሬቻ በዓላት በቂ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማዋ ነዋሪዎች መቅረብ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር  ወ/ሮ ሽታዬ መሀመድ ለሀገር ውስጥ ሚዲያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ኮሚሽኑ የገበያ ጥናትን መሠረት በማድረግ በበዓላት ወቅት በገበያ ላይ የሚፈጠረውን ፍላጎት በመለየት በቂ የፍጆታ ምርቶች እንዲቀርቡ በስፋት መስራቱን ገልጸዋል።

ወ/ሮ ሽታዬ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከአምራቾች፣ ከአስመጪዎች፣ ከዩኒየኖችና ከተለያዩ የኀብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመተባበር የምርት ትስስር በመፍጠር የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች፣ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች እንዲሁም እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች በበቂ መጠን መቅረቡን አስረድተዋል።

እነዚህ ምርቶች በከተማው በሚገኙ በዘመኑ 700 የሸማች ኀብረት ሥራ ማህበራት ሱቆችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በአዲስ ዓመት ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች፣ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እንዲሁም በ154 የኀብረት ሥራ ማህበራት ሱቆች በስፋት ለሸማቹ እየቀረቡ መሆናቸውን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።

ከነፃ ገበያው ጋር ሲነፃፀር በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡት እነዚህ ምርቶች የከተማዋን ነዋሪዎች የበዓል ፍላጎት በማሟላት የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና ገበያውን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በበዓሉ ወቅት 27/4 የሸማች ኀብረት ሥራ ማህበራት ሉካንዳ ሥጋ ቤቶች ሥጋን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ዝግጅት መደረጉን ወ/ሮ ሽታዬ ገልጸው፤ ይህም በበዓሉ ወቅት የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ዋና ኮሚሽነሯ በመጨረሻ ህብረተሰቡ ምርቶቹን ከኀብረት ሥራ ማህበራት ሱቆች፣ ከኤግዚቢሽንና ባዛር ማዕከላት እንዲሁም ከቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በመግዛት ከተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ኮሚሽኑም በበዓላት ወቅት የምርት አቅርቦትና የገበያ መረጋጋት ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ መከታተሉን አረጋግጠዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.