ለዓለም ከተሞች ምሳሌ የሆነች ከተማ - አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ዝቅተኛ የአደጋ ተጋላጭ የሆነች፥ ደህንነቷ የተጠበቀና የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋም ከተማ በሚል ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ሁለተኛ ከተማ ሆና ተቀምጣለች።
የጂኦስፓሻል ኩባንያ አልፋ ጂኦ በዋነኝነት በሶስት መመዘኛዎች የአዲስ አበባ ከተማን የመዘነ ሲሆን አካላዊ የአየር ንብረት ለውጥ፥ አደጋ ተጋላጭነት፤ሊገጥሙ ለሚችሉ አደጋዎች አስተዳደር እና ፖሊሲ ምላሽ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የማላመድ እርምጃዎች ላይ በማተኮር ነው ምዘናው የተካሄደው።
በእነዚህ መመዘኛዎች አዲስ አበባ ከተማ ከ72 ከተሞች ጋር ተወዳድራ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ለዓለም ከተሞች ምሳሌ ሆናለች፡፡
በዓለም የስልጣኔ ቁንጮ የተባሉትን እንደነ ፓሪስ እና ለንደን የመሳሰሉት ከተሞች አስከትላ በዓለም ላይ የአየር ንብረት ተጋላጭነት የምትቋቋም ከተማ በሚል ከአሜሪካዋ ቺካጎ ቀጥሎ በቁንጮ ላይ የተቀመጠችው አዲስ አበባ በኮሪደር እና የመንዝ ዳርቻ ልማት ያከናወነችው ስራዎች እና የዘረጋቻቸው ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች በዚህ ደረጃ እንድትቀመጥ አስችሏታል፡፡
አዲስ አበባ የዓለም ቀልብ የምትስብ ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ብቻ አይደለችም ከምቹነት ባለፈ የአደጋ ተጋላጭነቷ ዝቅተኛ የሆነች፥ ደህንነቷ የተጠበቀ የአየር ንብረት ለውጥን የምትቋቋም ከተማ ናት ፡፡
በዓለምአቀፉ ጂኦስፓሻል ኩባንያ አልፋ ጂኦ (Alpha Geo) ለአዲስ አበባ የተሰጠው ማረጋገጫ ለፖሊሲ አውጪዎች፤ ኢንቬስተሮች እና የመሰረተ ልማት ባለቤቶች አዲስ አበባ ከተማ በተመለከተ የውሳኔ ሀሳቦች ለመስጠት እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡
በዓለም ላይ የሚገኙ ከተሞች ፈጣን የህዝብ ቁጥር ጭማሪን እያስተናገዱ ሲሆን ይህ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት ማደግ አዳዲስ ፍላጎቶችን ይዞ የሚመጣ ሲሆን በዚያው መጠን ደግሞ ከተሞች ለሚፈጠሩ አዳዲስ ፍላጎቶች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባቸዋል፡፡
በዚህ መርህ የተቃኘው የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ እና የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋ በዓለማቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲቸራት እያደረገ ሲሆን በ8 ወንዞች 59 ኪሎ ሚትር ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለበርካታ ችግሮች ሁሉን አቀፍ ምላሽ የሰጠ ነው፡፡
ወንዞችን ማልማት ከመዋብ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት፤ የወንዞችን መበከል ይከላከላል፣ የጎርፍ አደጋን ይቀንሳል፣ የከተማዋን የሙቀት መጠን ይቀንሳል፥ ነዋሪዎች ንጹህ አየር የሚያገኙበትን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትን እና አዕምሮአቸውን የሚያድሱበትን ዕድል ይፈጥራል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.