መጭው የደመራና የመስቀል በዓል በሰላም ተከብሮ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

መጭው የደመራና የመስቀል በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲውል መላው የከተማው ነዋሪ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ።

የ2019 ዓ.ም የደመራ መስቀል በአል አከባበር ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በጋራ በመሆን የምክክር መድረክ ያካሄደ ሲሆን በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲያልፍና ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና የከተማው ነዋሪው ለበአሉ ሰላማዊነት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምራያ ጠቅላይ አዛዥ እንዳሉት የመስቀል በአል በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በድምቀት የሚከበርና ብዙ ህዝብ ወደ አደባባይ ሚወጣበት እንደመሆኑ የበአሉን አከባበር የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች እንዳይኖሩና ያለምንም ፀጥታ ችግር ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር በቂ የፀጥታ ዝግጅት የተደረገ መሆኑን ገልፀው በአሉ በሰላም እንዳያልፍ የሚፈልጉ ስለሚኖሩ እጅ ለእጅ በመያያዝ በጋራ ለሰላም በመቆም ለጠላት ሀይሎች ክፍተት ባለመፍጠር በአሉ በሰላም እንዲከበርና የሀገርን ገፅታ ለአለም ማሳወቅ ይገባል ብለዋል።

ጀኔራሉ አክለውም በአላቱ በዮኒስኮ በማይዳሰስ ቅርስ የተመዘገበ አለማቀፋዊ በአል እንደመሆኑ የሀገርን ገፅታ በሚገነባና አንድነትን ባጠናከረ መልኩ እንዲከበር በበአሉ ወቅት የተከለከሉና የተፈቀዱ የሚያዙ ነገሮችን የሀይማኖቱ የእምነት አባቶች ለምዕመናኑ በማስረፅ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ማድረግ ይጠበቃል ብለው የሀይማኖት አባቶችና የፀጥታ መዋቅሩ በቅንጅት እየሰሩ ያለውን አጠናክሮ በመቀጠል በአሉ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ሁሉም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

አቶ ተስፋዬ ደንድር የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቢሮ ኃላፊ ተወካይ እንዳሉት በአሉ በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ የሚያከብረው እንደመሆኑ ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆን በትኩረት የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በአሉ ያለፀጥታ ስጋት ሀይማኖታዊ ትውፊቱንና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲያልፍ በአንድነትና በቅንጅት ከሀይማኖቱ አባቶችና ከህዝቡ ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመው በዓሉ በሰላም እንዳያልፍና የቤተ ክርስቲያኒቱን ስርዓት ባልጠበቀ መንገድ እንዲሆን የሚያደርጉ አካላት በመከታተልና ጥቆማ በመስጠትና የተከለከሉ ህትመቶችና መሰል ጉዳዮችን ባለመያዝ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

መጋቢ ታምራት አበጋዝ የአዲስ አበባ ከተማ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ ምክክር መድረኩን በቪዲዮ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት የመስቀል ደመራ በአል በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ ትልቅ በአል ሲሆን በአሉ ከሀይማኖት በአልነቱ በተጨማሪ አለም አቀፋዊ እንደመሆኑ የሀገራችንን መልካም ገፅታ በሚያሳይ ፣ ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በሀይማኖት መሪዎች ሀይማኖታዊ ስርአቱንና በመንግስትም አስፈላጊውን ዝግጅት ተደርጓል ።

ዋና ፀሀፊው አክለውም በአሉ በዩንሲኮ በማይዳሰስ ቅርስ የተመዘገበ አለማአቀፋዊ በአል እንደመሆኑ የበአሉ አስተባባሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የመንግስት የፀጥታ አካላት በሰላም በመከባበርና ሀይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

መላከ ብርሀን ሰለሞን በቀለ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ እንዳሉት የደመራ መስቀል በአላት ከሀይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር የአንድነት፣ የመተሳሰብና የመከባበር በአል ሲሆን በአሉን ስናከብር የመስቀሉን ታላቅነት በማስቀደም አንድነት መሰረት በማድረግ ሀይማኖታዊ ትውፊቱንና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርና የሀገርን መልካም ገፅታ አጉልቶ ባሳየ መልኩ ፣ የሀይማኖት ተቋማት ከመንግስት የፀጥታ አካል ጋር የሚያስቀምጡትን ሂደት ምዕመኑ መከተልና ለበአሉ ሰላማዊነት በጋራ ኃላፊነትን መወጣት እንዳሚገባ አሳስበዋል።

"መንፈሳዊ በዓላት የሰላም ምልክቶችና የአንድነት ዓርማዎች" ናቸው በሚል ርዕሰ ጉዳይ በረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል አማካኝነት ጥናታዊ ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን አሁን ላይ ከበፊቱ በበለጠ መልኩ በዓላት ሲከበሩ ለውጦችና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉ የገለፁት ተሳታፊዎቹ የሀይማኖቱ ተከታዮች ፍጹም ጨዋነት በተሞላበት መልኩ እንዲከበር የበኩላቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

በማጠቃለያው መርሐ ግብር ላይ የሀገረ ስብከት ሀላፊዎች፣የደብር አስተዳዳሪዎች የጠቅላይ ቤተ ክህነት የደመራ በዓል ኮሚቴዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.