"እያንዳንዳችን የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

"እያንዳንዳችን የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እና ማንነት ቢኖረንም እንደ ደመራው በጋራ ስንቆም ጨለማውን የሚያሸንፍ ብርሃን እንሆናለን"! ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመስቀል አደባባይ እየተከናወነ በሚገኘው የመስቀል ደመራ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ ሁነቶች አንዱና የጋራ የባህል ሀብት መሆኑን ገልጸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና መስዋዕትነት የሰው ልጆች ከጨለማ ወደ ብርሃን እንዲሸጋገሩ የተደረገበት እውነት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፣ እምነቱ የሚያስተምረውን ይቅርታ እና ፍቅር ታሳቢ በማድረግ ዘላቂ ሰላም ያለው ማኅበረሰብ መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዓሉ በዩኔስኮ የተመዘገበ የሰው ልጅ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ በመሆኑ የሀገርን ገጽታ እና የባህል ሀብታችን ከፍ ያደረገ መኾኑን ጠቁመዋል። 

በደመራው ዙሪያ የሚበሩ ችቦዎች በአንድነት ሲሰበሰቡ አካባቢውን በብርሃን እንደሚሞሉ ሁሉ፥ ማኅበረሰቡም በልዩነቶች ውስጥ በሕብረት ሲቆም፣  ለሀገር የማይበገር ጥንካሬ እንደሚሆን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የዓለም የስህበት ማዕከልና የከተማ የለውጥ ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ እንደ መስቀል ያሉ ሁነቶች የከተማዋን እንግዳ ተቀባይነት እና ኢትዮጵያዊ ማንነት ለዓለም ማሳየት የሚቻልባቸው ኹነቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። 

እንደዚህ ያሉ ታላላቅ ሁነቶች በመዲናዋ በስኬትና በደማቅ ሁኔታ ሊከበሩ የቻሉት በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በመዘምራን፣ በወጣቶች፣ በበጎ ፈቃደኞችና በጸጥታ አካላት የተቀናጀ ትብብር መሆኑን ገልጸው፣ ለተደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት በአንድነት ደምቀን የምንበራበት፣ የተቀያየሙ የሚታረቁበት፣ በፍቅርና በጋራ ሥራ በሁሉም የኢትዮጵያ  አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.