ዛሬ የናይጄሪያን ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማንና ልዑካቸውን በመቀበል፣ በአዲስ አበባ በተግባር ላይ ስላለው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ያስመዘገብናቸውን ውጤቶች፣ ልምዶችና ተሞክሮዎች አካፍለናል።
ልዑካኑ በከተማችን የመደመር ትውልድ ግንባታ ሥራ አካል ሆነው በየሰፈሩ የተገነቡ የሕፃናት መጫወቻ ቦታዎችን፣ የሕፃናት ማቆያና እንክብካቤ ማዕከላትን፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና አገልግሎት ማዕከላትን እንዲሁም ለወላጆችና አሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ጎብኝተዋል። ጉብኝቱም ልምድና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ጠቃሚ ዕድል ፈጥሯል።
ኢንቨስትመንታችንን በመሠረተ ልማት ላይ ብቻ ሳንገድብ፣ በሰው ሕይወት፣ በተለይም በሕፃናት እድገት፣ ደህንነትና ደስተኛነት ላይ ቀዳሚ ትኩረት ከምንሰጣቸው የልማት ዘርፎች አንዱ ነው። ይህ ከማኅበራዊ ኃላፊነት በላይ፣ የመደመር ትውልድን ለመገንባት መሠረት የሚጥል ወሳኝ ኢንቨስትመንት ነው።
ፕሮግራሙን ስንጀምር በአዲስ አበባ የሕፃናት መጫወቻ ቦታዎች ብዛት 11 ብቻ ነበር። በሦስት ዓመታት ውስጥ ግን ቁጥራቸውን ወደ 6,000 አሳድገናል። በተመሳሳይ፣ የሕፃናት ማቆያ ማዕከላትን ብዛት ከ20 ወደ 1,200 አድርሰናል።
አዲስ አበባን ሕፃናት ለማደግ ፣ በአፍሪካ ተመራጭ ከተሞች ለማድረግ እየሠራን ነው። በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራማችን ባከናወንነው ሥራም፣ የእድገት ውስንነት የታየባቸውን ሕፃናት መጠን ከ13.5 በመቶ ወደ ቀድሞው መጠን አንድ አምስተኛ ዝቅ ማድረግ ችለናል።
በሕፃናት ላይ አተኩረን ስንሠራ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ እንገነባለን! የተሻለ ትውልድ መገንባት የሥራዎቻችን ሁሉ ማዕከል ነው።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.