የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አጠ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አጠናቀናል! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ! ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አጠናቀናል!

ለተከታታይ ሁለት ቀናት ስናካሂድ የነበረውን የከተማ አስተዳደራችንን የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አጠናቀናል።

በግምገማችንም በአንደኛው ሩብ ዓመት የከተማችን ነዋሪዎች የጣሉብንን እምነትና የሰጡንን ኃላፊነት በታማኝነት ለመወጣት በገባነው ቃል መሠረት፣ በነዋሪዎቻችን የኑሮ ሁኔታና ተጠቃሚነት ላይ ለውጥ ያመጡ፣ ለቀጣይ ሥራዎቻችንም መሠረት የጣሉ ውጤታማ ተግባራትን መፈጸም መቻላችንን ገምግመናል።

ለአፈጻጸማችን ስኬት መሠረት የሆኑት በከተማችን የተፈጠረው የሥራ ትጋት፣ በታማኝነት የማገልገል ባህል፣ በመደመር መርህ በፍጥነትና በጥራት የመፈጸም ልምድ እንዲሁም ጊዜን ሳናባክን ዕቅድን ወደ ተግባር የመቀየር አቅማችን ናቸው።

የመደመር መንግሥት ሥራዎችን አዲስ የፖለቲካ ባህል በሚፈጥር መልኩ ከመፈጸም ባሻገር፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን አደረጃጀት በማሻሻልና ውጤትን መሠረት በማድረግ አዳዲስ የአመራር ስምሪቶችን ማከናወን ችለናል።

በ90 ቀናት ዕቅዳችን የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራዎችን፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎችን፣ የቤቶች ግንባታንና የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን የማሻሻል ሥራዎችን አከናውነናል። የቤት ችግር ያለባቸውና በልማት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተነሱ ዜጎች ንጹሕና የዜጎችን ክብር የሚጠብቁ ቤቶች እንዲያገኙም ሠርተናል።

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ለመቀነስ የማዕድ ማጋራት ሥራዎችን አከናውነናል። በተጨማሪም፣ በክረምት ግንባታ አይከናወንም የሚለውን የቆየ አስተሳሰብ በመቀየር በርካታ ፕሮጀክቶችን ማከናወን ችለናል።

በትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዘርፍም አራት ትላልቅ የመኪና ማቆሚያና ተርሚናል ማዕከላትን ወደ ሥራ አስገብተናል። አዳዲስ መንገዶችን፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፣ የውሃ ማስወገጃና የፍሳሽ መስመሮችን በመገንባት በክረምት ወቅት የሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎችን ለመቀነስና በሰው ሕይወት ላይ ይደርስ የነበረውን የሞት አደጋ ለመከላከል ተጨባጭ ሥራዎችን ሠርተናል።

በክረምት ወቅት የሚኖረውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በሰባት የገበያ ማዕከላት ሰፊ የምርት አቅርቦት ወደ ከተማችን እንዲገባ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ሠርተናል። የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችንም ደረጃ ማሳደግ ችለናል።

እነዚህን ጨምሮ በሰው ተኮር ልማት ዘርፎች ያከናወንናቸው ተግባራት ማኅበራዊ ፍትሕን ከማስፈን አንጻር ጉልህ ሚና ነበራቸው። በተመሳሳይ፣ በተቋማትና በግለሰቦች መካከል የሚታዩ የአፈጻጸም ልዩነቶችን በድጋፍና በክትትል ሂደታችን ከመሠረቱ ለመፍታት እንሠራለን።

የምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ ከተቋም ግንባታ አንጻር ትኩረት የሚሹ ናቸው። የተበታተነ አቅም ራዕይን አያሳካም፤ ሀገርንም አይገነባም። ስለዚህ እያንዳንዱ ሠራተኛ በግልጽ የተለየ የሥራ ድርሻና ተጠያቂነት ኖሮት፣ በመደመር መርህ ተቀናጅቶ የሚሠራበትን አሠራር ማጠናከር ይጠበቅብናል።

የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም፣ የዜጎችን ክብር የሚጠብቅና ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ ሥራ እንሠራለን!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.