ከተማዋን የአፍሪካ የባህል፣ የኪነ-ጥበብና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው "አደይ ኮንቴምፖራሪ አርት አዋርድ" በአድዋ ድል መታሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐፍታይ ገብረእግዚአብሔር፣ ከተማዋን የአፍሪካ የባህል፣ የኪነ-ጥበብና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
"የኢትዮጵያ የፈጠራ ጥበባት አዲስ ገጽታ" የሚል መሪ ሐሳብን መሠረት ያደረገው መድረኩ፣ ጥንታዊ ባህልን ከዘመናዊ የፈጠራ ሥራዎች ጋር በማቀናጀት በድምቀት እየተከናወነ ይገኛል።
ከተማዋ ለሥነ-ጥበብ ዕድገትና ከፍታ የሰጠችውን ትልቅ ቦታ በተግባር ለማረጋገጥ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የባህልና የኪነ-ጥበብ መሠረተ ልማቶችን ገንብታ ለሥራ ማብቃቷን አስታውሰዋል።
ለአብነትም የአድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሁም በከተማዋ የተገነቡ የጥበብ፣ የቴአትርና የኤግዚቢሽን ማዕከላት መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በግልጽ የሚያሳዩ ህያው ምስክሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኃላፊው አያይዘውም፣ ይህ ሁሉ መሠረተ ልማት የተገነባበት ዋና ዓላማም፣ አዳዲስ ሐሳቦችን ለሚያፈልቁና ሀገራቸውን በፈጠራ ከፍ ለማድረግ ለሚተጉ ወጣቶች አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል።
"ጥበብ የህዝብ ነፍስ፣ የከተማችንም ህያው የመንፈስ መገለጫ ናት" ያሉት አቶ ሀፍታይ፣ በዕለቱ የቀረቡት የስዕል፣ የቅርጻቅርጽ፣ የፋሽን ዲዛይን፣ የሰርከስ፣ የዳንስና የሙዚቃ ሥራዎች የወጣቶችን ድንቅ የፈጠራ አቅም በግልጽ እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል።
መድረኩ በተለይም ለነባርና አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሚሰጠው የዕድሜ ልክ የክብር ውቅና ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ የመንፈስ ስንቅ የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
አቶ ሐፍታይ አክለውም፣ መድረኩ ተራ የሽልማት ስነ-ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ የጥበብ ባለሙያዎች የሚገናኙበት ልዩ ምሽት መሆኑንም ገልጸዋል።
መንግሥት ለጥበብና ለጥበበኞች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ በማንሳትም፣ ለአደይ ኢንተርቴይንመንት እና ፕሮሞሽን፣ ለተባባሪ አካላት፣ ለአዘጋጆች እንዲሁም ለተወዳዳሪዎች ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመድረኩ በየዘርፉ የላቀ ብቃት ላሳዩ ባለሙያዎች የሽልማት መርኃ ግብር ተካሄዷል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.