“የትግራይ ሕዝብ ሕልውና ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር የተቆራኘ አይደለም”፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የአንድን የፖለቲካ ድርጅት ሕልውና እና ደኅንነት ከሕዝብ እና ከሀገር ሕልውና ጋር ማቆራኘት መሠረት የሌለው፣ የተዛባ እና አደገኛ አስተሳሰብ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ የፖለቲካ ድርጅት ደኅንነትን ከሕዝብ ደኅንነት ጋር ማስተሳሰር የሕዝቡን ሕልውና በቀጥታ ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ በፍጹም ተቀባይነት የለውም።
ህወሓት ወደ ሃምሳ ገደማ ዓመታትን ያስቆጠረ ድርጅት መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የትግራይ ሕዝብ ግን ለሺህ ዓመታት በጽናት የኖረ እና ወደፊትም የሚኖር ሕዝብ መሆኑን አስረድተዋል።
ህወሓት ከ50 ዓመታት በፊት ያልነበረ እና በአሁኑ ወቅትም ታሪክ እየሆነ ያለ ድርጅት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከትግራይ ወጥቶ ኢትዮጵያን መምራትም አዲስ ነገር አለመሆኑን እና እንደ አፄ ዮሐንስ ያሉ ታላላቅ መሪዎች ከትግራይ ወጥተው ሀገር መምራታቸውን፣ እነርሱ ዛሬ ባይኖሩም የትግራይ ሕዝብ ግን ጸንቶ እንደሚኖር አብራርተዋል።
በመሆኑም ህወሓት እየከሰመ እንደሚሄድ፣ መሪዎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚነሱ እና እንደሚወድቁ፣ መንግሥታትም እንደሚለዋወጡ ጠቅሰው፣ ሕዝብ እና ሀገር ግን ሁልጊዜም ጸንተው እንደሚኖሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ የትግራይን ሕዝብ ከልማት እና ከሰላም አርቋል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አሸናፊ እና ተሸናፊ በእኩልነት የተስተናገዱበት ታሪካዊ አጋጣሚ እና በሀገራችን አዲስ የሰላም ምዕራፍ የከፈተ ቢሆንም ህወሓት የገባውን ቃል በማጠፉ ስምምነቱ እንዲደናቀፍ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፌዴራል መንግሥት በስምምነቱ መሠረት ተኩስ ከማቆም ጀምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ኃላፊነቱን በአግባቡ ቢወጣም፣ ድርጅቱ ግን ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ወደ መሣሪያ ግዢ እና ወጣቶችን በግዳጅ ወደ መመልመል መግባቱን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ እንዳብራሩት፣ ድርጅቱ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዳይመለሱ በመያዣነት ከመጠቀሙም በላይ የፌዴራል መንግሥት የጀመራቸውን የአየር ትራንስፖርት፣ የባንክ እና የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማስተጓጎል ሕዝቡ ላይ ዳግም ስቃይ አድርሷል ብለዋል።
መንግሥት ‘ጦርነት አያዋጣም፣ ሰላም ይሻለናል’ በሚል ተደጋጋሚ ምክር ቢለግስም፣ ቡድኑ ግን ምክሩን ወደ ጎን በመተው እና ከተለያዩ ኃይሎች ጋር በማበር ወደማያዋጣ ጦርነት መግባቱን ጠቁመዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት በስፋት እየተተገበረ ባለበት ወቅት፣ በትግራይ ግን አንድ ኪሎ ሜትር እንኳ የኮሪደር ልማት አለመከናወኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንጽጽር አቅርበዋል።
ድርጅቱ ለሕዝብ ልማት ከመሥራት ይልቅ፣ ለዕርዳታ የመጣን እህል ከተፈናቃዮች ጎሮሮ እየነጠቀ እና ማዕድናትን እየዘረፈ ድሮኖችን እና የጦር መሣሪያዎችን በመግዛት ላይ ተጠምዶ መቆየቱን አጋልጠዋል።
ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከባድ ድርቅ ተከስቶ እያለ፣ ቡድኑ ጦርነት በማወጅ እና የአየር ትራንስፖርት እንዲዘጋ በማድረግ ሕዝቡን ለከፋ ችግር መዳረጉ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ህወሓት ‘እኔ ከሞትኩ ትግራይ የለችም’ በሚል ከንቱ አስተሳሰብ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖር ቢጥርም፣ የትግራይ ሕዝብ ግን ይህንን መራራ ምዕራፍ አልፎ ወደ ልማት እና ሰላም እንደሚሸጋገር ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።
ሻዕቢያ ከጥፋት መልዕክተኝነት የማይመለስ ከሆነ መዘዙ እጅግ የከፋ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስጠነቀቁ
ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ጠላቶች መጠቀሚያ መሆኑን አቁሞ ለቀረበለት የሰላም እና የጋራ ልማት ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ የሚከተለው መዘዝ እጅግ በጣም ከባድ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ የኤርትራው ገዥ ቡድን (ህግደፍ) የራሱን ሀገር እና ሕዝብ የልማት ጥያቄ ወደ ጎን በመተው የቀጣናው የጥፋት ኃይሎች መናኸሪያ እና መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
"የራሱን ችግር ያልፈታ ኃይል ለሌላው ሊተርፍ አይችልም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የውጭ "አይዞህ ባዮች" ጥይት ከማቀበል ባለፈ የራሳቸውንም ችግር መፍታት እንደማይችሉ በመጠቆም፣ ሥርዓቱ ከልማት እና ከትብብር ይልቅ ቀጣናውን የማተራመስ አጀንዳን መምረጡ ፈጽሞ እንደማያዋጣው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
አገዛዙ በዚያች ሀገር ላይ ያስከተለውን ውድቀት በመጥቀስም፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከመገንጠሏ በፊት በንግድ እና በኢንዱስትሪ ደምቀው የነበሩት ከተሞቿ መደብዘዛቸውን አንሥተዋል።
በአንድ ወቅት ከ300 በላይ ፋብሪካዎች የነበሯትን ኤርትራን ወደ ባዶነት ከቀየረው እና ውቢቷን አስመራን አንሳ እንድትገኝ ካደረገው ሻዕቢያ ጋር መተባበር የጥፋት ጥግ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም ለሰላም እና ለጋራ ልማት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ልማትን ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ መሆንን የመረጠው የኤርትራ መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ ታቅቦ የልማት አጋር እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
ይሁን እንጂ ሻዕቢያ የውጭ ኃይሎችን ተማምኖ ይህን የሰላም መልዕክት "ጆሮ ዳባ ልበስ" ብሎ በጥፋት መንገዱ የሚገፋበት ከሆነ፣ በመጨረሻ የሚከተለው መዘዝ እጅግ መራራ እና የከፋ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.