በተሰጠው ማስጠንቀቂያና ግንዛቤ መሰረት ጥፋቱን ያላስተካከለው ተቋም 400 ሺህ ብር ተቀጣ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በዛሬው ዕለት ባካሄደው የቁጥጥር ስራ ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻን የበከለ ብርሃን ቦሌ ሸማቾች ህብረት ተቋም የ400,000 (አራት መቶ ሺህ) ብር የገንዘብ ቅጣት በመቅጠት አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል ።
ባለስልጣኑ ለህብረተሰቡ በተለያዩ አማራጮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም ጥፋቱ ማስቆም ያልቻለው ብርሃን ቦሌ ሸማቾች ህብረት ስራ የተባለው ድርጅት በቸልተኝነት ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻን ወደ ወንዝ እና አጎራባች ወደ ሆነው ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ግቢ በማገናኘት ሲለቅ ተገኝቷል።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በተሰጠው ማስጠንቀቂያና ግንዛቤ መሰረት ጥፋቱን እንዲያስተካክል ቢነገረውም ባለመስተካከሉ ምክንያት በደንብ ቁጥር 180/2017 ቅጣት ሰንጠረዥ 1 ተራ ቁጥር 6 መሠረት የ400,000 (አራት መቶ ሺህ) ብር የገንዘብ ቅጣት በመጣል አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶበታል እንዲሁም ህገ-ወጥ የፍሳሽ መስመሩ በአስቸኳይ እንዲስተካከል ተደርጓል።
ከተማዋን የማሳመርና የጽዳት ስራዎች ቀንና ሌሊት በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ባሉበት በዚህ ወቅት መሰል የደንብ መተላለፍ በሚፈጽሙ ህገ-ወጥ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚወሰደው ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለስልጣኑ አሳውቋል።
ህብረተሰቡም ማንኛውንም የአካባቢ ብክለት እና የደንብ መተላለፍ ሲመለከት በ 9995 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።
ዘገባው፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.