የአዲስ አበባ ልኳንዳ ቤቶች ማህበር የስጋ መሸጫ ዋጋ ላይ ቅናሽ አደረገ።
የማህበሩ አመራሮች ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ጋር ባደረጉት ቆይታ የማህበራቸውን ውሳኔ አሳውቀዋል።
የአዲስ አበባ ሉኳንዳ ቤቶች ማህበር አመራሮች በከተማዋ ከሚገኙ የስጋ ቤት ባለቤቶች ጋር ከተወያዩ በኋላ በአንድ ኪሎ የቁርጥ ስጋ ላይ የ500 ብር ቅናሽ አድርገዋል።
በውሳኔያቸው መሠረት በመዲናችን የሚገኙ ስጋ ቤቶች ከነገ 14/02/19 ዓ ም ጀምሮ አሁን ከሚሸጡበት የቁርጥ ስጋ ዋጋ 500 ብር ቀንሰው ለመሸጥ የወሰኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ማህበሩ ለንግድ ቢሮ በላከው ደብዳቤ 5000 ብር ይሸጥ የነበረ የቁርጥ ሰጋ 4500 ብር፣ 4500 የነበረ 4000 ብር እንዲሁም 4000 ብር ይሸጥ የነበረ የቁርጥ ስጋ 3500 ብር እንዲሸጥ መወሰኑን አሳውቋል።
እንደ ማህበሩ አመራሮች ገለፃ ወደ ቤት ይዘው መሄድ ለሚፈልጉ ደንበኞች ለወጥና ለጥብስ የሚሆን ስጋ በትላልቅ ቁርጥ ቤቶች ለማህበረሰቡ በኪሎ 2500 ብር እስከ ጠዋቱ 4:00 ለመሸጥ መወሰናቸውንም አሳውቀዋል።
የማህበሩ ውሳኔ ከዚህ ቀደም ስጋን በዝቅተኛ ዋጋ ሲሸጡ የነበሩ ልኳንዳ ቤቶችንና የሸማች ህበረት ስራ ማህበራት ሱቆችን የማይመለከት መሆኑን አመራሮቹ አሳውቀዋል።
የአዲስ አበባ ልኳንዳ ቤቶች ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወልደማርያም አባተ እንደገለፁት ማህበራቸው ከስጋ ተረፈ ምርት ጋር ተያይዞ ኤክስፖርት ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልፀው እነዚህ ስራዎች ሲሳኩ የስጋ ዋጋ ከዚህ በታች ይቀንሳል ብለዋል።
በከተማችን የሚገኙ ታዋቂ የስጋ ቤት ባለቤቶች ጭምር የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ማካሄዳቸውን የገለፁት አመራሮቹ የህብረተሰቡን ጥያቄና የመግዛት አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔው መወሰኑን አሳውቀዋል።
በመጨረሻም የተወሰነው ውሳኔ ወጥ የሆነ አፈፃፀም እንዲኖረው ቀድም ብሎ የተሰበሰበውን የዋጋ መረጃ መሠረት በማድረግ አፈፃፀሙን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እንዲከታተሉት የማህበሩ አመራሮች ጠይቀዋል።
የማህበሩን ውሳኔ ሁሉም ቁርጥ ቤቶች በወጥነት ተፈፃሚ ማድረግ ያለባቸው መሆኑ በመድረኩ የተገለፀ ሲሆን በየደረጃው የሚገኙ የንግድ ቁጥጥር ባለሙያዎች ውሳኔውን በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲያስፈፅሙ ክብርት ወ/ሮ ሀቢባ አሳስበዋል።
ውሳኔውን ተፈፃሚ በማያደርጉ ላይ ህብረተሰቡ በ8588 መረጃ በመስጠት የመፍትሄው አካል ሊሆን ይገባል ተብሏል።
ጥቅምት 13/2019 ዓ ም
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.