ወንዞቻችንን ወደ ሕይወት፣ ተፈጥሮን ወደ ውበት፣...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ወንዞቻችንን ወደ ሕይወት፣ ተፈጥሮን ወደ ውበት፣ አካባቢያችንን ወደ ቱሪስት መዳረሻነት እየቀየርን ነው!

የከተማ ልማት ማለት መሠረተ ልማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ ለነዋሪዎች ንጹሕና ምቹ አካባቢ፣ የመዝናኛና የማኅበራዊ ትስስር ዕድሎች፣ የሥራና የገቢ ምንጮችን መፍጠርም ጭምር ነው።

ዛሬ መርቀን ለህዝብ ክፍት ያደረግነው ከቀጨኔ፣ አምባሳደር፣ ኢሬቻና ባምቢስ እስከ ሰላም መንገድ የሚዘልቀው የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን በመንከባከብ አዲስ አበባን ለመኖር፣ ለመሥራትና ለመዝናናት ምቹ፣ አረንጓዴና ውብ ከተማ የማድረግ ጉዟችን አካል ነው።

በፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት ከ56,000 በላይ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል። አሁንም በንግድ፣ በአገልግሎት፣ በመዝናኛና በአረንጓዴ ልማት እንክብካቤ ለብዙ ዜጎች የሥራና የገቢ ዕድሎች እየተፈጠሩ ነው።

በተጨማሪም፣ በጎርፍ አደጋ ለመጋለጥ ተገደው የነበሩ ነዋሪዎቻችንን አዲስና ምቹ ወደሆኑ መኖሪያ ቤቶች በማሸጋገር ደኅንነታቸውንና የኑሮ ሁኔታቸውን ለማሻሻል ተችሏል። የግብርና ምርቶች ማቅረቢያ ማዕከላትን፣ የዕደ ጥበብ ምርት ማምረቻና መሸጫ ስፍራዎችን እንዲሁም ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትን በማዘጋጀት የአምራቾችን፣ የነጋዴዎችንና የሸማቾችን ትስስር እያጠናከርን ነው።

ለዚህ ውጤት ከሐሳብ ማመንጨት ጀምሮ አቅጣጫ በመስጠትና በማበረታታት ለደገፉን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን፣ በጥናት፣ በዕቅድ፣ በግንባታና በቅንጅት ለደከሙ የከተማችን አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ አማካሪዎችና ተቋራጮች ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በተለይም ለልማቱ መሳካት በትብብርና በመተማመን ከጎናችን ለቆማችሁ ነዋሪዎቻችን ያለኝን ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና እገልጻለሁ። የዛሬው ውጤት የጋራ ጥረታችንና የትብብራችን ፍሬ ነው።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.