የ2018 የግብር ዘመን የንግድ ትርፍ ግብር ማሳ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የ2018 የግብር ዘመን የንግድ ትርፍ ግብር ማሳወቂያና መክፈያ ጊዜ ጥቅምት 30 ይጠናቀቃል።

​የ2018 የግብር ዘመን የደረጃ "ሀ" ዓመታዊ የንግድ ትርፍ የማሳወቂያና የመክፈያ ጊዜ ጥቅምት 30/2019 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ሲሆን ግብር ከፋዮች የመጨረሻ ቀናትን ሳይጠብቁ ግብራቸውን አሳውቀው በወቅቱ እንዲከፍሉ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።

​ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ እንዳስታወቁት፣ አሁን ላይ የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች የንግድ ትርፍ የማሳወቂያና የመክፈያ ጊዜው እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች የግብር ማሳወቂያና መክፈያ ጊዜ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም እንደነበር በማስታወስ በዚህም አብዛኞች ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ መወጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች ደግሞ ከሐምሌ 1 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30/2019 ዓ.ም ድረስ እንዲያሳውቁና እንዲከፍሉ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

​ቢሮው ከ2018 ዓም ጀምሮ ወራዊ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እና ደሞዝ የማሳወቅና ክፍያ የመፈጸም ተግባርን ሙሉ በሙሉ በኦንላይን ማድረጉን የገለፁት አቶ ሰውነት ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮችን ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ግብር የማሳወቅና የመክፈል ሂደት ሙሉ በሙሉ በበይነ-መረብ (ኦንላይን) እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት ግብር ከፋዮች በአካል ወደ ቢሮ መምጣት ሳያስፈልጋቸው የሂሳብ መዝገቦቻቸውን በሲስተም አማካኝነት በመላክ፣ ተጨማሪ አስፈላጊ ሰነዶችን ደግሞ ቃለ መሐላ በፈጸሙበት የኢሜይል አድራሻ መላክ ይጠበቅባቸዋል፡፡

​የኦዲት ስራው ተከናውኖ የክፍያ ማዘዣ በሲስተሙ ሲላክላቸውም ባሉበት ሆነው ክፍያቸውን በኦንላይን መፈጸም የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ግብር ከፋዩ በአካል መምጣት የሚጠበቅበት በኦንላይን ለፈፀመው ክፍያ ደረሰኝ ለማወራረድ ካሸሪ ጋ ብቻ እንደሆነ ተጠቁሟል።

አሰራሩ ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ የግብር ከፋዮች እንግልት፣ ወረፋና ምልልስ በመቅረፍ የግብር ከፋዮችን በአገልግሎት አሰጣጥ የነበሩ ቅሬታዎችን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ ታስቦ የተዘረጋ እንደሆነም አቶ ሰውነት ገልጸዋል።

​በመሆኑም ግብር ከፋዮች በመጨረሻዎቹ ቀናት ከሚያጋጥሙ የሲስተም መጨናነቅ፣ ወረፋና መጉላላት እንዲሁም በወቅቱ ባለመክፈል ከሚመጣ ቅጣት ለመዳን ቀሪዎቹን ጥቂት ቀናት በመጠቀም በኦንላይን አሳውቀው በኦንላይን እንዲከፍሉ ማሳሰቢያ ተላልፏል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.