ዛሬ የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶብሶች ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ ተለውጠው ሥራ ላይ በመዋላቸው የተሰማኝን ደስታ መግለጽ እፈልጋለሁ።
ባለፉት ጥቂት ወራት የተፈጥሮ ጋዝ ምርትን ከሚመረትበት ስፍራ ወደ አዲስ አበባ የማጓጓዝ፣ የጋዝ ማደያዎችን የማዘጋጀት እና የከተማ አውቶብሶችን ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመለወጥ ሰፊ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ይህ ታሪካዊ እርምጃ በነዳጅ ግዢ ላይ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ ያስቀራል። በተጨማሪም የሕዝብ ትራንስፖርት የሥራ ማስኬጃ ወጪን በመቀነስ የዜጎችን የጉዞ ታሪፍ በግማሽ ያቃልላል። በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በራስ አቅም ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመለወጡ ተግባር ደግሞ የሀገር ውስጥ አቅምንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
በቀጣይም በነዳጅ ላይ ያለንን ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት እና ሀገር ውስጥ እያመረትን ያለነውን የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ 400 አዳዲስ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ አውቶብሶች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ። በምግብ፣ በቤት እና በትራንስፖርት ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ሥራዎችን በማከናወን በዜጎች ሕይወት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተጀመሩት አበረታች ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.