የከተሞች ልማት የዜጎችን ሕይወት ከፍ ማድረግ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ እንደ ስሟ በየጊዜው እያበበችና አዲስ እየሆነች በመጣች ቁጥር የዜጎቿን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረች፣ የጋራ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠች ትገኛለች።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የተገነባውን የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ የተቀናጀ የመኖሪያ መንደር መርቀው ለተጠቃሚዎች አስተላልፈዋል።
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ተደምረን ከሠራን፣ ተደምረን ካሰብን ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን ያሉ ሲሆን፣ የከተሞች ልማት ከተሞችን ውብና ተወዳዳሪ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን ሕይወት ከፍ ማድረግ ነው በማለት ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ዩኒቨርሲቲ ግንባታ እውን የሚሆንበት መሬት ሲዘጋጅ፣ ለዚህ ታላቅ ብሔራዊ እሳቤ ሲሉ ቦታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮች ዛሬ የክብርና የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤቶች ሆነዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዕለቱ ለአርሶ አደሮቹ ምትክ ዘመናዊ የመኖሪያና የመሥሪያ ቦታዎችን ሲያስረክቡ፣ የልማቱ ትርጉም ከቤት ግንባታና ስጦታ የዘለለ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።
ልማት ማለት የሰውን ኑሮ ማክበር፣ አብሮነትን ማጠናከር እና የነገን ትውልድ በስልጣኔ ማነጽ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኑሮ እየዘመነ መሄዱ ግድ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ሰፊ መሬት በተናጠል ይዞ ከመኖር ይልቅ፣ ተደምሮና ተቀራርቦ መኖር የኑሮ ጥራትን ከፍ እንደሚያደርግና የሰውን ልጅ ክብር እንደሚያስጠብቅ አስገንዝበዋል።
ለአርሶ አደሩ የተዘጋጀው ዘመናዊው የመኖሪያ መንደር ሁሉን አቀፍ ምቾትን የጠበቀ ሲሆን፣ ንጹህ አየር እና ለልጆች የሚመች ሁኔታን የፈጠሩ ዘመናዊ መኖሪያና መሥሪያ ቤቶችን አካትቷል።
ይህ የልማት ማዕቀፍ ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ የመሥሪያ ሱቆች፣ የእህል መጋዘኖች፣ ወፍጮ ቤቶች እና አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን ያለአንዳች የትራንስፖርት እንግልት በቀጥታ የሚሸጡበትን ሥፍራ ጨምሮ ሌሎች የኢኮኖሚ ማዕከላትን የያዘ ነው።
ከዚህም ባሻገር ግብርናን ከዘመናዊነት ጋር ለማጣጣም የሚያስችሉ ለአርሶ አደሩ የተዘጋጁ ዘመናዊ የከብቶች ማደለቢያ ሼዶችም ተገንብተዋል።
የሕፃናት ማቆያዎች፣ የስፖርት ሜዳዎች እና የዕድሜ ባለጸጎች የእርጅና ክብር የሚጠበቅባቸው ማኅበራዊ ትስስር ማጠናከሪያዎች በዚሁ ሰፊ ሥፍራ ውስጥ ተካተዋል።
አዲስ አበባ ዛሬም በወንዝ ዳርቻዎቿና በመልሶ ማልማቷ አዲስ ውበትን እየተጎናጸፈች ስትገኝ፣ የዚህ ለውጥ ባለቤቶች የሆኑት አርሶ አደሮችም፣ በዘመናዊው የመኖሪያ መንደር የነገ ተስፋቸውን ጀምረዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.