አዲስ አበባ ፤ በዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

አዲስ አበባ ፤ በዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት መድረኮች ተከታታይ እውቅና እያገኘች ያለች ከተማ!

ከተማን መለወጥ የሚቻለው በግልጽ ራዕይ፣ በተቀናጀ ጥረትና የሰው ልጅን ሕይወት ማዕከል ባደረገ የልማት አቅጣጫ ነው። አዲስ አበባም ይህንን እሳቤ በተግባር እየተረጎመች መሆኗን በዓለም አቀፍ መድረክ ዳግም አስመስክራለች።

በቅርቡ በቻይና ሻንሃይ ከተማ በተካሄደው የ2026 የሻንሃይ ዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት ሽልማት ውድድር፣ አዲስ አበባን ጨምሮ አምስት ከተሞች ተሸላሚ ሆነዋል።

በዘንድሮው የሻንሃይ ሽልማት እውቅና ያገኙት፦

1. አዲስ አበባ (ኢትዮጵያ)
2. ሳንቲያጎ ዴ ካሊ (ኮሎምቢያ)
3. ኢስታንቡል (ቱርኪዬ)
4. ጂንግዴዠን (ቻይና)
5. ካቶቪስ (ፖላንድ) ናቸው።

ይህ ሽልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአራተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን፣ አዲስ አበባ በአራቱ ዙሮች ሁለት ጊዜ እውቅና አግኝታለች። በ2024 የሴኡል ስማርት ሲቲ ሽልማትን፣ በ2026 ደግሞ የሻንሃይ ዓለም አቀፍ የዘላቂ ከተማ ልማት ሽልማትን አግኝታለች።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በ2023 አዲስ አበባ በምገባ ፕሮግራምና በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ዘርፎች ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ያለች ከተማ በመሆኗ ዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት አግኝታለች።

ይህ እውቅና ለሀገራችን ታላቅ ክብር ከመሆኑም በላይ፣ እየሠራን ላለነው ሥራ ብርታትና ተጨማሪ ተነሳሽነት የሚሰጥ ነው። ከሁሉም በላይ፣ በከተማችን የምንተገብራቸው ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃና የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል የምናደርገው ጥረት፣ እንዲሁም የከተማዋን የተፈጥሮና ማኅበራዊ ፀጋዎች ወደ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የመቀየር ሥራችን ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የሚያረጋግጥ ዓለም አቀፍ ምስክርነት ነው።

የመደመር እሳቤያችንም ልማትን ከሰው ሕይወትና ደኅንነት ጋር አጣምሮ ያያል። ከተሞች የሥልጣኔ መገለጫ እንዲሆኑ፣ ያላቸውን ፀጋዎች በመለየትና በማልማት፣ የሰውን አቅም ከተፈጥሮና ከኢኮኖሚያዊ ሀብቶች ጋር በማቀናጀት ለጋራ ብልፅግና መሥራትን ይጠይቃል።

በከተማችን የልማት ጉዞ እስካሁን የተጓዝነው ርቀት ጠንካራ መሠረት የጣለ ቢሆንም፣ የሚቀረን ረጅም ጉዞ እንዳለ እናውቃለን። ሀገራችን ኢትዮጵያም ለዘመናት ከተጫኗት ድህነትና ልዩ ልዩ ችግሮች በዘላቂነት ለመላቀቅ፣ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣትና ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር የጀመረችው ጉዞ ፍሬ እያፈራ ይገኛል። ሆኖም ይህንን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ወደ ተሟላና ዘላቂ ለውጥ ለመቀየር የሁሉንም ዜጎች ርብርብ፣ ቁርጠኝነትና ተሳትፎ ያስፈልጋል። ስለሆነም ሁላችንም ለለውጡ በቁርጠኝነት መትጋት ይገባናል።

ያገኘነውን ዓለም አቀፍ እውቅናም እንደ መዳረሻ ሳይሆን፣ እንደ ተጨማሪ ኃላፊነትና ለበለጠ ሥራ ማበረታቻ እንወስደዋለን።

ይህንን ተነሳሽነት በመያዝ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች የሥልጣኔና የብልፅግና መሠረት እንዲሆኑ እንሠራለን። አቅሞቻችንን በመደመር፣ ፀጋዎቻችንን ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር፣ ክብራችንን የሚመጥን የብልፅግና ግብ ለመድረስ ትጋታችንን እናጠናክራለን።

ከተሞቻችን የመደመር ሥልጣኔ መዳረሻ፣ ለነዋሪዎቻቸው ምቹና ተስማሚ የኑሮ አካባቢ፣ ለቀጣዩ ትውልድም ዘላቂ የብልፅግና ውርስ እንዲሆኑ በጋራ እንሠራለን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.