የአፍሪካ ሴሌብሬትስ 2026 ፌስቲቫል በአዲስ አ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የአፍሪካ ሴሌብሬትስ 2026 ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ተከፈተ

የአፍሪካ ሴሌብሬትስ 2026 (Africa Celebrates 2026) ፌስቲቫል በአዲስ አበባ በይፋ ተከፍቷል። ፌስቲቫሉ የአፍሪካን ባህል፣ ኪነ-ጥበብ፣ ፈጠራና ሥራ ፈጣሪነት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና በሌሎች አጋር ተቋማት ትብብር እየተካሄደ ይገኛል።

ከህዳር 2 እስከ ህዳር 6 ቀን 2019 ዓ.ም በሚቆየው ፌስቲቫል ከ45 የአፍሪካ ሀገራትና ከ17 ሌሎች የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ የባህልና ሃይማኖት መሪዎች፣ አርቲስቶች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችና ሌሎች የተለያዩ ዘርፍ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የዘንድሮው ፌስቲቫል “አንዲት አፍሪካ፣ አንድ ህዝብ፡ ባህልን፣ ፈጠራን እና ስራ ፈጣሪነትን ለጋራ የበለፀገ የወደፊት ጊዜ ማስተሳሰር” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ሲሆን፤ የአፍሪካን ባህላዊ፣ የተፈጥሮና የሰው ኃይል እምቅ አቅም ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመቀየር ያለመ ነው።

በፌስቲቫሉ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር፤ አዲስ አበባ የዚህ ፌስቲቫል ቋሚ መነሻና መካሄጃ መሆኗን ገልጸዋል::

ኃላፊው አዲስ አበባ የነፃነት አርማ የሆነው ታላቁ የአድዋ ድል የተመዘገበባት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተባትና ታላላቅ የዲፕሎማሲ ማህበረሰቦች መገኛ መሆኗን በማስታወስ፤ “በአድዋ ላይ አፍሪካ ልትሸነፍ እንደማትችል አረጋግጣለች። ዛሬ ደግሞ የእኛ ሀላፊነት አፍሪካ ልትከፋፈል እንደማትችል ማረጋገጥ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም ‘አፍሪካ ሴሌብሬትስ’ ታሪክን ብቻ ከማውሳት ባለፈ በኪነ-ጥበብ፣ በባህል፣ በቅርስ፣ በቴክኖሎጂ እና በንግድ ዘርፎች ወጣት ፈጣሪዎችን ከፖሊሲ አውጪዎች፣ አርቲስቶችን ከባለሀብቶች ጋር የሚያገናኝ የጋራ ብልፅግና መድረክ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል ከተማዋ እያካሄደች ያለውን የኮሪደር ልማት፣ አዳዲስ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎችና የዘመናዊ እንግዳ ተቀባይነት ዘርፍ ማሻሻያዎችን በማንሳት፤ የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ከስብሰባ አዳራሽ ወጥተው ከተማዋን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።

“በአድዋ ድል መታሰቢያ ቆማችሁ ታሪክን አስታውሱ፤ በብሔራዊ ሙዚየም ሉሲን ጎብኙ፤ አዲስ አበባን ከእንጦጦ ተራራ ላይ ሆናችሁ ተመልከቱ፤ አንድነት ፓርክን ጎብኙ፤ እንዲሁም እንኳን ደህና መጣችሁ በምንልበት የቡና አፈላል ስነ-ስርዓታችን ተሳተፉ” በማለት ተሳታፊዎቹ የከተማዋን ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል። ተሳታፊዎቹ ወደየሀገራቸው ሲመለሱም ስለ ኢትዮጵያ በጎ ምስክርነት እንዲሰጡ አደራ ብለዋል።

ፌስቲቫሉ እስከ ህዳር 6 ቀን 2019 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ በቀጣይ ቀናት በአፍሪካ ባህል፣ በኪነ-ጥበብ፣ በቅርስ፣ በፈጠራ ኢንዱስትሪዎችና በሥራ ፈጣሪነት ዙሪያ የተለያዩ ውይይቶችና መርሃ ግብሮች ይካሄዳሉ።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.