የሌፕዚግ ከተማ ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎችን ጎበኙ
ከጀርመን ሀገር የሌፕዚግ ከተማ የመጡ የልዑካን ቡድን አባላት በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች እና የተገኙ ውጤቶችን ጎብኝተዋል።
ሌፕዚግ ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር የእህትማማች ከተማ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ ሁለቱ ከተሞች በ“NAKOPA – Inclusive Future (IFU) Leipzig–Addis Ababa Project” በተሰኘው የትብብር ፕሮጀክት ላይ በጋራ እየሠሩ ይገኛል። ፕሮጀክቱ በተለይም ወደፊትን ታሳቢ ያደረገ የትምህርት (Future-Oriented Education) እና የከተማ ፕላን አዘገጃጀት (Urban Planning) ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በሁለቱ ከተሞች መካከል የልምድ፣ የእውቀትና የተሞክሮ ልውውጥን ለማጠናከር ያለመ ነው።
የልዑካን ቡድኑ በጉብኝቱ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎችን በመመልከት፣ ከተማዋን ዘመናዊ፣ ለኑሮ ምቹ፣ አረንጓዴና ለሁሉም ነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶችን ተመልክተዋል።
በተለይም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎችን ለማስፋፋት፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን ለማሻሻል፣ አረንጓዴ ሥፍራዎችን ለማበልጸግ፣ የወንዝ ዳርቻዎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽና ለመዝናኛ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎች የልዑካን ቡድኑን ትኩረት የሳቡ ሲሆን፣ በልማት ሥራዎቹም ላይ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ጉብኝት በአዲስ አበባና በሌፕዚግ ከተሞች መካከል ባለው የእህትማማች ከተማ ግንኙነት የልምድና የእውቀት ልውውጥን ከማጠናከር ባለፈ፣ በዘመናዊ የከተማ ልማት፣ በዘላቂ የከተማ ፕላን እና በአካታች ልማት ዘርፎች የጋራ ተሞክሮን ለማጎልበት ያለውን አስፈላጊነት ያመላክታል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.