አቅርቦት ተኮር የገበያ ማረጋጋት አስተዳደር ስርዓት የነዋሪዎችን ኑሮ እያሻሻለ ነዉ፡- ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ የገበያ ማረጋጋት፣ ህገወጥ የንግድ ቁጥጥር እና አዲስ አበባ ታምርት ግብረ-ኃይል በ45 ቀናት ያከናወኗቸዉን ተግባራት አፈፃፀም በገመገሙበት ወቅት ነዉ፡፡
እንደ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ገለፃ ከማዕከል እስከ ወረዳ በተዋረድ የተዋቀረዉ ግብረ ኃይል የኑሮ ዉድነት ማቅለያ ስትራቴጂካዊ አማራጮችን በመጠቀም ለነዋሪዎች ጥራት ያለዉ፣ የተመጣጠነና ተደራሽነትን ማዕከል ያደረጉ ምርቶች ቀርበዋል፤ ነጋዴዎችም ህግና ስርዓትን ተከትለዉ እንዲያቀርቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል አያይዘውም ከማዕከል እስከ ወረዳ የተዋቀረዉ ግብረኃይል ባለፉት 45 ቀናት ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ስጋ፣ ዳቦ፣ ልዩ ልዩ ሸቀጦች፣ እና የእህል ምርት አቅርቦት እንዲኖር የላቀ አስተዋፅዖ አድርጓል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው በከተማዋ የገበያ ማረጋጋት ስራ ቀጣይነት እንዲኖረዉ ነጋዴዎች ከህግና ከአሰራር ውጭ እንዳይሆኑ ከንግድ ሰርቪላንስ፣ ከገቢዎች ሰርቪላንና ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር ገቢን ለማሳደግና ልማትን ለማስቀጠል ተናበን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ከህብረት ስራ ማህበራት ሱቆችና ከአምራቾች ጋር በመሆን ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረብን ነዉ ብለዋል፡፡ ለኢንዱስትሪዎችም ውሃና የመብራት አቅርቦት እንዲመቻች ተደርጓል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል የገበያ ማረጋጋት ስራዉ ቀጣይነት እንዲኖረዉ መደበኛ ያልሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ተጠያቂ ማድረግ፣ የቅዳሜና እሁድ ገበያ ማዕከላትን አስፍቶ መስራት፣ የገበያ ማረጋጋት ስራ በህብረተሰቡ ዘንድ ያመጣው ውጤታማነት ከፍላጎትና ከአቅርቦት አንፃር ተንትኖ ማቅረብ የቀጣይ የዕለት ተዕለት ተግባር ሆነዉ ይቀጥላሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የገበያ ማረጋጋት፣ ህገወጥ የንግድ ቁጥጥር እና አዲስ አበባ ታምርት ግብረ-ኃይል አካላትም በቀጣይ የ90 ቀናት በሚከናወኑ ተግባራት የጋራ ግንዛቤ ወስደዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.