"በጎነት"ብለን በሰየምነው የመኖሪያ መንደር የተገነቡ ሁለት ባለ 9 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎችን እና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላትን መርቀን ለ140 አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኛ ነዋሪዎች አስተላልፈናል።
በልደታ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆርቆሮ ሰፈር በሚባለው የተጎሳቆለ የመኖሪያ መንደር ይኖሩ ለነበሩ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ማየት ለተሳናቸው፣ ለተለያየ ማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ እና በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች ያስተላለፍናቸው ምቹ የመኖሪያ ቤቶች ሳሎን፣ መኝታ ቤት፣ የማብሰያ እና የመጸዳጃ እንዲሁም የመኝታ ክፍሎች ያላቸው ዘመናዊ ቤቶች ናቸው።
በዚህ የበጎነት መንደር ካስተላለፍናቸው የመኖሪያ ቤቶች ጋር በማቀናጀት የእናቶችን ጫና የሚያቀል የህጻናት ማቆያ፣ ለአካባቢው እናቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ፣ የሚሰሩ እጆችን ከስራ የሚያገናኙ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎኖችን እንዲሁም የልብስ ስፌት ማሽኖችን አዘጋጅተን ለነዋሪዎቹ የስራ እድል ፈጥረናል።
በመኖሪያ መንደሩ ቤት ለሰጠናቸው ማየት የተሳናቸው ነዋሪዎች እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ኬኖች፣ ለአካል ጉዳተኛ ነዋሪዎች ደግሞ ክራንችና ዊልቸሮችን አዳርሰናል።
ሰርቶ ካገኘው ላይ ለወገን በጎ ለመስራት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ቤቶቹን የገነባውን ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በራሴና በነዋሪዎቹ ስም እያመሰገንኩ፣ በጎነት አያጎድልምና ፈጣሪ ጨምሮ እንዲሰጠው እመኛለሁ።
የሚሰሩ ልማቶች ሁሉ ለሰው ልጆች ተስፋ የሚሰጡ እና የኑሮ ጫናን የሚያቃልሉ ይሆኑ ዘንድ ሰው ተኮርነታችን በተግባር የሚገለጽ ነው።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.