35ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ው...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

35ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የ2ኛ ዙር የከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የተፈረመውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በብድር የተገኘው 207,200,000 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የሳኒቴሽንና ሃይጂን አገልግሎት ተግባራትን ለማሻሻልና የዘርፉን የማስፈጸም አቅም ለማጠናከር የሚውል ነው፡፡ ብድሩ ወለድ የማይታሰብበት፣ 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት ሆኖ 6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ብድሩ ከአሀራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የንብረት ታክስ በከተሞች ነዋሪ በሆነው ሕዝብ መካከል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማስፈን፤ የመንግስት አገልግሎቶችን በተሻለ ጥራትና በዘመናዊ ዘዴ ማቅረብ ለማስቻል እና የከተማ መሰረተ ልማት ማሻሻያዎችን በቀጣይነት ለመተግበር የሚወጣውን የኢንቨስትመንት ወጪ በንብረት ዋጋ ማደግ ምክንያት በሚጣል ታክስ አማካኝነት ለመሰብሰብ የሚያስችል ነው፡፡ አዋጁ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ተፈጻሚነት የሚኖረው ሲሆን፤ ክልሎችም ይህንን አዋጅ መሰረት በማድረግ ከተጨባጭ ሁኔታቸው ጋር በተጣጣመ አኳኋን የየራሳቸውን የንብረት ታክስ ህግ እንዲያወጡ ያስችላል። በዚሁ መሰረት ይህንን ለማስፈጸም የሚረዳ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. በ3ኛ ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሪፎርም እና የካፒታል ማሳደጊያ ዕቅድ ላይ ነው፡፡ የባንኩን የሀብት ጥራት ለማሻሻል እና በአስተማማኝ መልኩ የካፒታል መጠኑን በማሳደግ ለኢኮኖሚው ዕድገት እና ልማት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ዘላቂነት ባለው መልኩ ተግባራዊ እንዲያደርግ ለማስቻል የሚረዱ የውሳኔ ሃሳቦች ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርበዋል፡፡ እነዚህም የባንኩን አስተዳደራዊ ውጤታማነት ማጎልበት፤ የሂሳብ መግለጫዎቹን ጠንካራና ተቀባይነት ባለው መልኩ እንዲዋቀር ማድረግ እና የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የሚረዳ የመንግሥት የፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻል የሚሉ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ በማሻሻያ እቅዱ ላይ ተወያቶ ወደቀጣይ ተግባር እንዲገባ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ 

4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ባለፉት 16 ዓመታት በስራ ላይ የቆየው አዋጅ ሁሉንም የልማት ተዋናዮች ያሳተፈ የብልጽግና ዕቅድ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮና መርሆች አንጻር፣ ከአቻ ማዕከላዊ ባንኮች መልካም ተሞክሮ፣ከገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማነት እንዲሁም በፋይናንስ ራስን ከመቻል አንጻር ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ፤ ባለፉት አመታት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጦች በመኖራቸው፤ የባንኩን ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት የማስፈን፣ ዋጋን የማረጋጋት እና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የማድረግ ተልዕኮ ለማሳካት አዋጁን ማሻሻል እንደሚገባ ስለታመነበት ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ 

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በሁዋላ ግብአቶችን ታክለው ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ 

5. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ስለባንክ ስራ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ባለፉት አመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ፣ የአደረጃጀትና የአሠራር እና የመንግስት ፖሊሲ ለውጦች በመኖራቸው፤ ሀገራችን ለረጅም ጊዜ ዝግ አድርጋው የነበረውን የባንክ ስራን ለውጭ ሀገራት ክፍት ማድረጓን ተከትሎ ይህንን ለመምራት፣ የፍቃድ አሰጣጥን ለመወሰን እና ለማስተዳደር የሚያስችል የህግ እና የቁጥጥር ስርአት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን ታክለውበት ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

6. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የልማት ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት የአካባቢና ማህበረሰብ ተጽእኖ ግምገማና ጥናት እንዲካሄድባቸው በማድረግ ተጽእኖዎቹን አስቀድሞ በመተንበይ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ መተግበር ስላለባቸው ስራዎች የሚደነግግ እና የአካባቢ ጥበቃ ቁጥጥር አሰራርን በተቀናጀ መልኩ ስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ወጥ የሆነ ሀገራዊ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ 

 

 


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.