ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በተመለከተ

በበጀት ዓመቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ቀውሶች ተቋቁማ እና ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር በሁሉም መስኮች አስደማሚ ስኬት አስመዝግባለች፡፡የእዳ ጫናን ለማቃለልም ከፍተኛ ስራ ተከናውኗል፡፡ አሁን ላይ ያለብንን የእዳ ጫና ከአገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር ወደ 17 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህንን አሃዝ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እየሰራን ነው፡፡

ገቢ አሰባሰብን በተመለከተ

"ባለፉት 11 ወራት መንግስት 466 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ችሏል፡፡ ይህም ከተያዘው እቅድ አንጻር የ96 በመቶ አፈጻጸም አለው፡፡ ነገር ግን ይህ ከኢትዮጵያ አገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር 7 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ ግብር መሰወር መኖሩን አመላካች ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ ነው፡፡ ይህንን ጥረትም ዜጎች ሊያግዙ ይገባል፡፡"

ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾችን በተመለከተ

በተያዘው በጀት ዓመት ከምርትና አገልግሎት ወጪ ንግድ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ከሐዋላ አገልግሎትም 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ገቢ ተገኝቷል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም በምስራቅ አፍሪካ ትልቋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሳቢ አገር ናት፡፡ በበጀት ዓመቱም 3 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች፡፡ ስንዴን ጨምሮ በተኪ ምርቶችም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው፡፡ ለአብነትም በበጀት ዓመቱ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል፡፡

የፋይናንስ ዘርፉን በተመለከተ

"የፋይናንስ ሴክተሩ በበርካታ አመላካቾች ጤናማ ሂደት ውሰጥ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ12 ሺህ 800 በላይ የባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ዜጎችም የባንክ ደብተር አውጥተው እየተጠቀሙ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይመለስ ብድር አማካኝ አሃዝ 5 በመቶ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ግን 4 ነጥብ 5 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ከዓለም አማካኝ ያነሰ ነው፡፡ ባንኮች ከሚያቀርቡት ብድር ከ80 በመቶ በላይ የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚ ነው፡፡ ይህም የፋይናንስ ዘርፉ በጤናማ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ባንኮች ከአገር ውስጥ ባለፈ ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ከወዲሁ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡"

የኑሮ ውድነትን በተመለከተ

"የኑሮ ውድነት የበርካታ ሀገራት ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡በአንዳንድ ሀገራት ከ60 በመቶ በላይ የደረሰ የዋጋ ንረት እየተመዘገበ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ መንግስት በርካታ ኢንሸቲቮችን ቀርጾ እየሰራ ነው፡፡ በተለይ የሌማት ትሩፋት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ይገኛል፡፡ምርታማነትን ማሻሻልም ሌላኛው ስራ ነው፡፡ በዘንድሮው ዓመት ከዓለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር ከ100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰብ ተችሏል፡፡በተጨማሪም መንግስት 10 ቢሊዮን ብር ገቢ በመተው መሰረታዊ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ አድርጓል፡፡ ይህ ሁሉ የሚከናወነው የኑሮ ውድነቱ ዜጎቻችን ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለል ነው፡፡ በዚህም የዋጋ ንረቱን ባለፈው ዓመት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 23 በመቶ ዝቀ ማድረግ ተችሏል፡፡"

የግብርና ግብዓትን በተመለከተ

"ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳባሪያ ከውጭ ታስገባለች፡፡ ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከሚወጣው ወጪ ባሻገር ለአርሶ አደሩ ለማጓጓዝ ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪ ይጠይቃል፡፡ መንግስት ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ በዘንድሮው ዓመት ስራው ቀደም ብሎ ነው የጀመረው፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም 13 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መጓጓዝ ተችሏል፡፡ ቀሪ 2 ሚሊዮን የሚሆነው ጅቡቲ ደብ እየደረሰ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያ በምርጥ ዘር አቅርቦት እራሷን ለመቻል እየሰራች ነው፡፡ በመስኖ ልማትም ትልቅ እምርታ እየተመዘገበ ነው፡፡ ለአብነትም በዘንድሮው ዓመት ብቻ 40 ሺህ የሞተር ፓምፕ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል፡፡"

ትምህርትን በተመለከተ

"የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግስት ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ በዚህም 30 ሺህ የሚሆኑ አዳዲስ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን በርካታ ተማሪዎችም የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የትምህርት ስርዓቱ አካታች እንዲሆንም ዘመናዊ የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ ነገር ግን አገራዊ ለውጡን ተከትሎ አንድም ዩኒቨርሲቲ አልገነባንም፡፡አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲዎች ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው ጥራትን ማረጋገጥ ላይ ነው፡፡"

ጤናን በተመለከተ

"በዘንድሮው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል 10 ሚሊዮን ክትባት ተሰጥቷል፡፡ የኩፍኝ ወረርሽኝን ለመከላከልም በ58 ወረዳዎች ክትባት ተሰጥቷል፡፡ የወባ አጎበር ስርጭትም ተከናውኗል፡፡ በተለይ የመድሃኒት አቅርቦትን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከ8 በመቶ ወደ 36 በመቶ ማደረስ ተችሏል፡፡"

የለውጡ ሂደትን በተመለከተ

"ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ያደረጉ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ፤ አንደኛው ነባር ችግሮች ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ወቅታዊ ስብራቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ነባር ችግሮችን በአገራዊ ምክክር እና ሽግግር ፍትህ ለመፍታት እየተሰራ ነው፡፡ በምክክሩ ነገን የተሻለ ለማድረግ የምንሰራበት ሲሆን፤ ያለፉ በደሎችን ደግሞ በሽግግር ፍትህ የሚፈቱ ይሆናል፡፡ ወቅታዊ ችግሮችን ደግሞ በተቋማት ሪፎርም እየተፈቱ ይገኛሉ፡፡ከዚህ አኳያ ለተመዘገቡ ስኬቶች እውቅና እየሰጠን የሚቀሩትን ደግሞ በጋራ መስራት አለብን፡፡"

ሰላምን በተመለከተ

"ኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት በግጭትና ጦርነት አዙሪት ውስጥ አልፋለች፡፡ ይህ የመገዳደል ታሪክ በእኛ ትውልድ ሊቆም ይገባል፤ መንግስት ለሰላም የሚከፈል ማነኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው፡፡ባለፉት ጊዜያትም መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ በሆደ ሰፊነት በርካታ ርቀት ተጉዟል፡፡ በግጭትና ጦርነት ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን መያዝ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ለኢትዮጵያ ዛሬም ነገም የሚበጀው በሰላምና በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ነው፡፡"

ህግ ማስከበርን በተመለከተ

"ሶስት ክላሽ ሲይዙ አራት ኪሎ ይታያቸውና ውርውር የሚሉ አካላት፤ ትንሽ ሲቆነጠጡ ደግሞ ጀኖሳይድ ይላሉ፡፡ ይህ ተገቢነት የለውም፡፡ መንግስት በሰለጠነ መንገድ ችግሮች በውይይትና ድርድር እንዲፈቱ ቅድሚያ መስጠቱን እንደ ድክመት የሚቆጥሩ ካሉ፤ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ነው፡፡"

የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ

"የፕሪቶሪያው ስምምነት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ረገድ የባህል ለውጥ ያመጣንበት ነው፡፡ ተኩስን በማቆም አገልግሎትን በማስጀመር ትልቅ ድል አግኘተንበታል፡፡ ባንኮች፣ አየር መንገድ፣ ቴሌኮምን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል፡፡ በስምምነቱ መሰረትም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ ጀምረናል፡፡ ይህ ጅምርም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡"

ሙስናን በሚለከት

"ሌብነት ነቀርሳ ነው፤ ሀገርን ይበላል፡፡ ትንሽም ሆነ ትልቅ ሌብነት መጥፋት አለበት፡፡ ለዚህም ነው መንግስት የህግ ማሻሻያዎችን እያደረገ ያለው፡፡ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ግለሰቦች በህገ ወጥ መንገድ በርካታ ቢሊዮኖችን ያንቀሳቅሳሉ፤ ይህን መጠየቅ የሚችል ህግ አልነበረንም፡፡ አዋጁ ይህን ችግር በመቅረፍ የህግ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ነገር ግን አዋጁ ያጠቃናል ያሉ ሌቦች ከወዲሁ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ህዝብን ለማደናገር እየሞከሩ ነው፡፡ በመሆኑም ሌብነትን በመታገል ረገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተግባር የተጨበጠ ስራ ማከናወን አለበት፡፡"

ዲፕሎማሲን በተመለከተ

"ኢትዮጵያ የደም መሰዋትነት በመክፈል ጭምር ለሶማሊያ ሰላም ሰርታለች፤ አሁንም ለሶማሊያ የምንመኘው ሰላምና ልማት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎት እያስመዘገበች ካለው የኢኮኖሚ እድገት አንጻር የባህር በር ማግኘት ብቻ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ የትኛውም አካል ሳይጎዳ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በውይይት እውን ማድረግ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄም ተገቢና ቅቡልነት ያለው ነው፡፡ በዚህ ላይ ጥያቄ ካለም እርስ በርስ በመነጋገር መፍታት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ችግሮቻቸውን በሰላም እንዲፈቱ ገለልተኛ በሆነ አግባብ እንዲፈታ እየሰራች ነው፤ ይህንንም አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡"

ለኢትዮጵያዊያን የሚያስፈልጉ ስድስቱ “መ” ዎች:-

1) መወያየት- ችግሮችን ከግጭት ይልቅ በውይይት መፍታት

2) መትከል- ከችግኝ ባሻገር ለኢትዮጵያ የሚበጁ ተቋማትን በመትከል ሀገርን ማጽናት

3) መታደስ- እሳቤዎቻችንና አኗኗራችንን ወቅቱን በዋጀ መልኩ ማደስ

4) መሰብሰብ- ግብርን ጨምሮ ለህዝብ ጥቅም የሚውሉ ገቢዎችን መሰብሰብ

5) መነጠል- ከክፉ ሃሳብን፣ ከዘረኝነት እና ከሰፈርተኝነትን መነጠል

6) መዘጋጀት- አሁናዊ ሁኔታዎችን በሚዋጅ መልኩ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ማዘጋጀት ፤ ለዚህ ደግሞ እርስ በርስ ማገር በመሆን አገርን ማጠናከር  ይገባናል ብለዋል፡፡

 

 


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.