"የምትተክል ሃገር፣ የሚያጸና ትውልድ!"ከንቲባ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

"የምትተክል ሃገር፣ የሚያጸና ትውልድ!"ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዛሬ ማለዳ የ5ኛ ዙር አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን በከተማችን ከሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች፣ የዓለምአቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አትሌቶች፣ የተለያዩ ስፖርት ቤተሰቦች እንዲሁም ከከተማችን ነዋሪዎች ጋር በመሆን አስጀምረናል።

አረንጓዴና ውብ አካባቢን ለመፍጠር፣ በተፈጥሮ የበለጸገችና ከአየር ብክለት የፀዳች አዲስ አበባን ለትውልዱ ለማዉረስ ቃላችንን በተግባር መንዝረን ከነዋሪዎቻችን ጋር በመሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ባደረግነው ርብርብ የከተማችንን አረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2.8 በመቶ ወደ 17 በመቶ ከፍ ማድረግ ችለናል።

በኮሪደር ልማታችንም አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ስንተክል ከርመናል።

ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻዎቻችን የከተማችን ነዋሪዎች ፆታ፣ እድሜ፣ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት እንዲሁም ሃይማኖት ሳይገድባቸው የከተማዋን ተፈጥሯዊ ሚዛን መጠበቅ የሚችሉ ሀገር በቀል ዛፎችን፣ ለገፅታ ድምቀት የሚሆኑ የውበት እፅዋቶችን እንዲሁም የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞችን ተክለዋል።

ዘንድሮም በከተማችን 20 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ታሪክ ለመስራት የተዘጋጀን ሲሆን መላው የከተማችን ነዋሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዚህ ታላቅ ሃገራዊ ጥሪ ላይ በመሳተፍ ለትውልድ የሚሆን አሻራችሁን እንድታኖሩ ጥሪ አቀርባለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ

ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.