"አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ ማገናኘት ጥቅሙ ለሁለቱም በመሆኑ የገበያ ሰንሰለቶችን በማሳጠር ሁለቱን ወገኖች ማቀራረብ ተያይዞ ለማደግ ያግዛል ፤ ህብረብሔራዊ አንድነትንም ያጠናክራል !" አቶ ሞገስ ባልቻ
በጋራ ለመስራት እና ክልሎችን ለማስተሳሰር ያለመ የሁሉም ክልሎች የህብረት ስራ ተቋማት፡ ዩኒየኖች እና ሸማች ማህበራት የተሳተፉበት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በአዲስ አበባ አዘጋጅነት ተካሄደ።
የለውጡ መንግስት አንድ የኢኮኖሚያዊ እና የፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባት የተቀመጠውን ህገ መንግስታዊ አቅጣጫ የሚያጠናክሩ ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን ወስዷል።
ከእነዚህ እርምጃዋኛ መካከል በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ህዝባችንን ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በህግም በአሰራርም የተደገፍ ስትራቴጂካዊ ስራዎች ተከናውነዋል።
ፓርቲያችን ምርታማነት ላይ አንፀባራቂ ድል በማስመዝገብ በህዝባችን መካከል ተባብሮ ማደግ እንዲጎለብት ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች እንዲፈጠሩ ፤ ወንድማማችነት እህትማማችነት እና ህብረ -ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጦ ቃሉን በተግባር እየተረጎመ ይገኛል።
የህዝባችን ኢኮኖሚያዊ ትስስር መጥበቅ ተያይዞ ለማደግ ለሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል ነው ።
ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ በተሰሩት ስኬታማ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች ቢመዘገቡም በአንድ በኩል ተፈጥሯዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ፣ ቀጠናዊ እና አገራዊ ችግሮች በሌላ በኩል ደግሞ ሳይሰሩ ለመክበር በሚዘረጉ የገበያ ሰንሰለቶች አማካኝነት የኑሮ ጫናው በተለይም በዝቅተኛ ገቢ በሚኖረው ህዝባችን ላይ በርትቷል።
መንግስታችን እና ፓርቲያችን በሰው ተኮር ፕሮግራሞች የህዝባችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋጥ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር አምራቹ እና ሸማቹ የህብረተሰብ ክፍል በቀጥታ የሚገናኙበትን የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉት።
ለአብነትም በከተማችን አዲስ አበባ በአምስቱም የከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች ግዙፍ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት በሁሉም አቅጣጫ የሚመጣ ምርት በቀጥታ ለሸመቹ እንዲደርስ አበረታች ጥረቶች ተጀምረዋል።
በከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች የእሁድ ገበያን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ተግባርም ዋነኛ ዓለማው የኑሮ ውድነቱ ጫና በህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለማቃለል ነው።
የከተማ አስተዳደሩ በከተማች የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በመፈተሽ ፣ የአሰራር እና የአመራር ስርዓታቸውን እንዲፈትሹ የተሰካ ሪፎርም እንዲያደርጉ ተገቢውን እገዛ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
የከተማችን የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ከክልሎች አምራች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወሰዱ የቆዩ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ከሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የመጡ አመራሮች እና የህብረት ስራ ማህበራት ተወካዮች ከከተማችን ከፍተኛ አመራሮችና ከሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በብልፅገና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በምክክሩ መክፈቻ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር ከለውጡ በኋላ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሪፎርም ስራዎች ተቀርፀው መተግበራቸውን የጠቀሱ ሲሆን በተለይም የገበያ ስርዓቱን መስመር ለማስያዝ የተከናወኑ ሪፎርሞች ከኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አውስተዋል።
የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመጣጣም ከተፈጥሯዊ ፣ ሰው ሰራሽ እና ዓለም አቀፍ ችግሮች ጋር ተዳምረው በህዝባችን ላይ የፈጠሩትን የኑሮ ጫና ለመቅረፍ የአሰራር ስርዓቶች እየተፈተሹ እየተስተካከሉ መሆናቸውን ያመላከቱት ሀላፊው ኢትዮጵያ መሬቷ የሰጡትን አብቃይ አርሶ አደሮቿ እና አርብቶ አደሮቿ ታታሪ በመሆናቸው በአምራቹና በሽመቹ መካከል ያለውን ሰንሰለት ማሳጠር ችግሩን በእጅጉ እንደሚያቃልለው ገልፀዋል።
አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ ማገናኘት ጥቅሙ ለሁለቱም በመሆኑ የገበያ ሰንሰለቶችን በማሳጠር ሁለቱን ወገኖች ማቀራረብ ተያይዞ ለማደግ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ ህብረ - ብሔራዊ አንድነትንም ስለሚያጠናክር በመረጃ መረብ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ አቶ ሞገስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በምክክር ፕሮግራሙ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ/ ቤት ም/ ሀላፊ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ ፣ የኢፌዴሪ የህብረት ስራ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ አብዲ ኡመር ፣ የክልል አመራሮችና የህብረት ስራ ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች የከተማችን ከፍተኛ አመራሮችና የህበረተሰብ ተወካዮች ተካፍለዋል።
ከምክክሩ ባሻገርም የውይይቱ ተሳታፊዎች ታሪክንና ጥበብን አጣምሮ የያዘውን የአድዋ ድል መታሰቢያ ፣ የከተማችንን ገፅና እየቀየረ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት፣ ግዙፉን የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል እና ሌሎችንም የልማት ስራዎች በመጎበኘት ተቀናጅቶና ተናቦ የመስራትን አኩሪ ስኬት መገንዘብ ችለዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.