በአራት ቀን በተደረገ ቁጥጥር በተለያዩ ጥፋቶች ላይ የተገኙ ከ31ሺ በላይ ደንብ ተላላፊዎች ተከሰው መቀጣታቸውን አዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው የሚደርሰው የመንገድ ላይ ትራፊክ አደጋ በሰው ህይወትና አካል ላይ የሚያደርሰውን አሰቃቂ ጉዳት ቀጥሏል። በዚህም በርካቶች ለከፋ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል ። ከዚህም ባሻገር በንብረቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት ተባብሶ ቀጥሏል። በ2016 ዓ/ም ከደረሰው አጠቃላይ አደጋ በንብረት ላይ የደረሰው አደጋ 34ሺ 047 ሲሆን በንብረት ላይ የደረሰው አደጋ ከአጠቃላይ አደጋው 89 ፐርሰንቱን እንደያዘ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በንብረት ላይ ከደረሱ አደጋዎች መካከል በኮሪደር ልማት የተገነቡ መንገዶችንና መንገዶችን ለማስዋብ የተሠሩ መሠረተ ልማቶች ጭምር ጉዳትን እንዳስተናገዱ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በአደጋው እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ ቢሆንም የአጥፊዎች ቁጥር አለመቀነሱ አሳሳቢ ነው ያለው አዲስ አበባ ፖሊስ ሐምሌ 18 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ/ም ባሉ አራት ቀናት ውስጥ በቀንና በምሽት በተደረገ ቁጥጥር በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ጉዳት ያደረሱ ፣ ከመጠን በላይ ጠጥተው የተገኙ ፣ ካለ ደረጃ ሲያሽከረክሩ የተገኙ 31 ሺ893 አጥፊዎች ክስ ተመስርቶባቸው መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ከተቀጡት መካከል ለከተማችን መልካም ገጽታ ያላበሱ እና ለትራፊክ ፍሰቱ መሳለጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የመሰረተ ልማት አውታሮችና መንገዶቹን ለማስዋብ በውድ ዋጋ የተገዙ ስማርት ፖሎች፣ የተተከሉ ዘንባባዎች እና ሌሎች ተክሎች ላይ ጉዳት ያደረሱ አሽከርካሪዎች ይገኙበታል። አዲስ አበባ ፖሊስ በመሰረተ ልማት አውታሮቹ ላይ ጉዳት ያደረሱ አሽከርካሪዎችን አልኮል ጠጥተው የተገኙትን ፣ በተከለከሉ ቦታዎች ላይ ተሽከርካሪዎችን በማቆም ለፍስቱ መጨናነቅ ምክንያት የሆኑትን ጨምሮ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ውድ ዋጋ ያላቸው ስማርት የመንገድ ላይ ፖሎችን ፣ ውብ ዘንባባዎችንና ሌሎች ልማቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ አጥፊዎች የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ መደረጉን ያስታወቀው ፖሊስ
ሆን ብለው ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦችም በወንጀል እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ እንደተሰራ እና በቀንም ሆነ በምሽት የሚያከናውነውን የቁጥጥር ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ👇👇👇https://linktr.ee/addisababacommunication
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.