የአፍሪካ ፣ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ መግቢያ በር የሆነው የቦሌ መንገድ የኮሪደር ልማት ስራችን ከተማችንን በሚመጥን ገጽታ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን አካትቶ ሌላ ብስራት እና ተጨማሪ ድል ሆኖ ተጠናቋል::ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ሰፊ የመኪና ፣ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ ፣ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎች፣ የታክሲ እና አውቶቢስ መጫኛ/ማውረጃዎች፣ የህዝብ መናፈሻዎች፣ አረንጏዴ ስፍራዎች ፣ ፋውንቴይኖች፣ የህዝብ መጸዳጃ ስፍራዎች እንዲሁም የከተማችንን ፕላን የጠበቀ የቀለምና የመብራት ስራን አካትተን እጅግ በተዋበ መንገድ ገንብተን ለህዝብ አገልግሎት እነሆ ብለናል::
ይህ ስራ እንዲሳካ ከጅማሮው ከጎናችን የነበራችሁ አካላት በተለይም ህንጻችሁን ለእግረኞች እንዲሆን እና በተሰጣችሁ ዲዛይን በማደስ ከጎናችን የነበራችሁ የህንጻ ባለቤቶች ፣ 24/7 ስራውን ያስተባበራችሁ በየደረጃው ያላችሁ የከተማችን አመራሮች ፣ ኮንትራክተሮች ፣ አማካሪዎች ፣ የጉልበት ሰራተኞች እንዲሁም በመንገድ ስራው ምክንያት አመቺ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባልነበረበት ወቅት በፍጹም ትዕግስት ስታበረታቱን ለነበራችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉ ክብርና ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ::
እንዲህ ውብ ተደርጎ የተገነባውን መሰረተ ልማት መላው የከተማችን ነዋሪ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በባለቤትነት መንፈስ እንዲንከባከብ እና እንዲጠብቅ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ አዲስ እንደ ስሟ ውብና አበባ ለማድረግ በላቀ ትጋትና ታማኝነት ማገልገላችንን እንቀጥላለን::
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.