ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት እና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ዙሪያ ተወያዩ
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከንግዱ ማህበረሰብ አባላት እና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በተገኙበት መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱን አስመልክተው ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ እንደገለፁት ሪፎርሙ ለሀገራችን በርካታ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የሪፎርም ማሻሻያው በዋነኛነት ዘላቂ ልማትንና አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመገንባት፣ የመንግስትን የእዳ ጫና ለመቀነስ፣ የተረጋጋ ተወዳዳሪ እና የዋጋ ግሽበትን መቀነስ የሚያስችል የገበያ ሁኔታን ለመፍጠር እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ተኪ ምርቶችን በማምረትና ለውጪ ገበያ የሚላከውን ምርት በማሳድግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመፍጠር የውጪ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እድል እንደሚፈጥር አንስተዋል።
ወቅታዊ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር ደሃው እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ እንዳይጎዳ የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ መጨመር፣ ደሃውን መደጎም ፣ በተለይም በሴፍቲኔት የታቀፉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ገቢ በሚያስገኝና ተረጂነትን በሚቀንስ መንገድ የመደገፍ ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ሪፎርሙ በትልቁ ሊያግዙን የሚችሉ ሶስት አቅጣጫዎችን የምንከተል ሲሆን ይኸዉም በብዛት ማምረት በዚህ ለማምረት ደግሞ የልማት ትሩፋት ስርዓታችንን እና ሒደታችንን ማሻሻልና ለከተማዉ ህዝብ የሚጠቅሙ ምርቶችን በበቂ ማምረት ነዉ ብለዋል።
ሌላዉ የተመረቱ ምርቶች ጥራትና ደረጃቸዉን ጠብቀዉ ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ ማድረግና በወጪ ምርቶች መተካት እንደሚገባ ገልፀዉ እነዚህ ጥራት ያላቸዉ ምርቶች በዉጪ ገበያ ተፈላጊነት እንዲኖራቸዉ በገበያ በበቂ በማቅረብ ተወዳዳሪነታቸዉን መጨመር አለብንም ብለዋል።ይህም አንዱ የሪፎርሙ አካል በመሆኑ በከተማችን ዉስጥ መንቀሳቀስ አለብን ብለዋል።
እንዲሁም የስራ እድልን በስፋት መፍጠርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚተገበር መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም ከአምራቾች እና አስመጪዎች ጋር በቅርበት በመስራት እንዲሁም ገበያውን የሚያዛቡ፣ በተለይም ምንም ከውጪ ምንዛሪ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር እና ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራ ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.