በመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ እጥረት እንዲፈጠ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ እጥረት እንዲፈጠር ምርት ደብቀው በተገኙ ህገወጦች ላይ እርምጃ ተወሰደ፡፡ እርምጃው ተጠናክሮ እንዲሚቀጥል አዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

መንግስት የማክሮ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ መሻሻያውን ተከትሎ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር ግንዛቤ ማስጨበጥን ጨምሮ ልዩ ልዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከአምራቾች እና ከአስመጪዎች ጋር ወይይት መደረጉ ይታወቃል፡፡ 

 ምርቶችን በመደበቅ እና ሰው ሰራሽ የሸቀጥ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ በምርቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር እና ህግ የማስከበር ስራ መስረት በአዲስ አበባ ፖሊስ በአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ፣ የከተማው ገቢዎች ቢሮ ፣ ንግድ ቢሮና ደንብ ማስከበርን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ እና ግብረ ኃይሉ በማክሮ የኢኮኖሚ መሻሻያ ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን ከመስራት ጎን ለጎን ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር ምርቶችን በሚደብቁ ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ባደረገው ክትትል በጉለሌ ክፍለ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ሙሉጌታ መናፈሻ አካባቢ መጋዘን ሙሉ የምግብ ዘይት መያዙ ታውቋል፡፡ ዘይቱን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገበው ድርጅት ምርቱን በወቅቱ ወደ ገበያ ማቅረብ እንዳለበት እና በጉዳዩ ዙሪያ አስፈላጊውን ማስረጃ እንዲሰጥ ተጠይቆ እንዳላቀረበና ዘይቱ ወደ ሌላ ስፍራ በማጓጓዝ ላይ እያለ ሦስት አይሱዙ በግብረ ኃይሉ አማካኝነት ተይዞ በተደረገ ብርበራ መጋዘን ሙሉ ዘይት እና ወደ ሌላ ስፍራ ሊጓጓዝ የነበረ 7 አይሱዙ የታሽገ ዘይት እንደተያዘ አዲስ አበባ ፖሊስ ጨምሮ ገልፆል፡፡ ጉዳዩም እየተጠራ መሆኑ ተገልፆል፡፡

በተመሳሳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተደረገ ክትትል 8ሺ ባለ 3ሌትር እና 1ሺ924 ባለ አምስት እና 128 ባለ አንድ ሌትር ዘይት እንዲሁም 25 ኩንታል ተደብቆ ተይዟል፡፡ በክፍለ ከተማው ምርት የደበቁ ፣ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ የዋጋ ንረት እንዲባባስ ያደረጉ 73 ንግድ ቤቶች እንዲታሸጉ ተደርጓል፡፡

የግንዛቤ ችግር ሳይኖርባቸው ያልተገባ ተግባር ሲፈፅሙ በተገኙት ላይ እርምጃ ከመወሰድ ባሻገር የግንዛቤ እጥረት ያለባቸውን ደግሞ ከስህተታቸው እንዲታረሙ ግንዛቤ እያስጨበጠ መሆኑን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡   

ወደፊትም ክትትልና ቁጥጥሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ግብረ ኃይሉ አስታውቆ ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት በኩል እያደረገ ያለውን ድጋፍ ሊያጠናክር እንደሚገባ መልእክት ተላልፏል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.