እየተከልን እናንብብ
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሥልጣኔዎችን በተለያዩ አካባቢዎችና በተለያዩ ዘመናት አስተናግዳለች፡፡ ሁሉም ለዚህች ሀገር ዛሬ ያበረከቱት ዕሴት አለ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ለማለት በሚቻል ሁኔታ ለሦስት እልፍ ዓመት ጥቂት ፈሪ ዘመን ያህል አንድ ወጥ የመንግሥት ሥርዓትና የሕይወት ዘይቤ ውስጥ የኖሩ ናቸው፡፡ በዘመን ጅማሬ የደመቀና ገናናው ሥርዓት ሃልዮታዊ ማሕቀፍን መቀየር ባለመቻሉ የመንግሥታት ገናናነት በየዘመናቱ እየኮሰመነ የማኅበረሰቡም ኑሮ እየወየበ እንዲመጣ ምክንያት ሆነ፡፡
መቶ ዓመት ያልተሻገረው ዘመናዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት፣ አስተሳሰባዊ ማሕቀፎቹ እንከን የበዛባቸውና ያልጠሩ በመሆናቸው፣ በዘመናዊው ዓለም ወደ ኋላ አስቀርቶናል፡፡ ሕጸጽ በበዛባቸውና በዋናነትም ከውጭ በተኮረጁ አስተሳሰቦች ለመምራት በተደረገው ጥረት፣ ኢትዮጵያ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ስትናጥ ቆይታለች፡፡ መሪዎቿ ለሕመሟ የማይሆን መድኃኒት እየጋቷት ተፈራርቀዋል፡፡
እናም ዛሬ ላይ ሕመሟን በሚገባ የተረዳ እና በዘላቂነት የሚፈውሳት ሐኪምና መድኃኒት ትፈልጋለች፡፡ ሆኖም ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው እንዳይሆን፣ የሀገራችን ሕመም ውስጣዊ ነውና መድኃኒቱም ውስጣዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ያልተገባው መድኃኒት ሌላ ሕመም እያመጣበት ስትሰቃይ ኖራለችና፡፡ ከጭንቅና ከመከራ ለመገላገለል በፈለገችበት ወቅት ተገቢውን መድኃኒት አግኝታ አታውቅም፡፡ የወሰደችው እያገረሸባት ወይም ተጨማሪ ሕመም እየፈጠረባት ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡
መደመር ለምን? ለምን አሁን አስፈለገን? ብለን እንጠይቅ፡፡ የተቃርኖ ትርክቶቻችን ዕዳን እንጂ በረከትን ሊያወርሱን አልቻሉም፡፡ የተውሶ ትርክቶቻችን ለነጠላ ቡድናዊ ፍላጎት ጥቅም አስጠበቁ እንጂ ለጋራ ሀገራዊ ልዕልናችን አልጠቀሙንም፡፡
የተውሶ ዕሳቤዎች የትውልዶችን ዕዳ ከማራዘም የዘለለ ፋይዳ አላመጡም፡፡ አስተሣሣሪ ታሪክና ሥልጣኔ ቢኖረንም አስተሣሣሪ ትርክት ጠፍቶ ደም አፋሳሽ ሀገር አፍራሽ ትርክቶች ዋጋ አስከፈሉን፡፡ አዲስ አስተሳሰብ፤ አዲስ መንገድ፤ አዲስ ትርክት አስፈለገ፡፡ መደመር ተወለደ፡፡ ተነጣጥለን ወድቀናል፡፡ ተደምረን የትርክትን ዕዳ በትርክት በረከት ለመቀየር መደመር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የግድ ነው፡፡
ዳንኤል ክብረት፤ የትርክት ዕዳና በረከት፤ 2016፤ ገጽ 522-523
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.