በበጀት ዓመቱ የመንግሥት እና የህዝብ አቅሞችን...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በበጀት ዓመቱ የመንግሥት እና የህዝብ አቅሞችን አስተባብረን መስራት በመቻላችን ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ችለናል ፦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ለተከታታይ ሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች የ2016 አፈፃፀም ግምገማ እና የ2017 ዕቅድ አቅጣጫ ውይይት ዛሬ ተጠናቅቋል። 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ማጠቃለያ ወቅት ለተነሱ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ዙሪያ ማብራሪና የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል። 

ከንቲባዋ በማብራሪያቸው የ2016 በጀት ዓመት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያጠናከርንበት፣ በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም እውን የሆነበት፣ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችን በትኩረት በማድመጥ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እና ሰው ተኮር ስራዎችን በማስተሳሰር የህዝባችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የቻልንበት ነው ብለዋል። 

በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ማንንም ወደኋላ ያልተው ናቸው ያሉት ከንቲባ አዳነች በሁሉም የለውጥ መስኮች አሳታፊ እና አካታች የልማት አቅጣጫን በመከተል የከተማችን ነዋሪዎች አኗኗር በመሰረታዊነት የሚለውጡ ስራዎች ማከናወን ችለናል ብለዋል። 

 ለአብነትም የትውልድ ግንባታ አካል የሆነውን የቀዳማዊ ልጅነት መርሀ ግብር በመዘርጋት የልጆች እና የእናቶች ጤናን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን በመግለጽ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄም አካታችና ጥራት ያለውን ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

የሴቶችንና የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ለ300 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን፣ ከተማን እንደ አዲስ የመገንባት ያህል ፋይዳ ያለውን የመጀመሪያ ዙር የኮደር ልማቱን ውጤታማ በሆነ አግባብ መጠናቀቁን ያነሱት ከንቲባዋ አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስና አበባ እስኪትሆን ድረስ የተጀመረው የኮሪደር ልማቱ የህዝባችን ተሳትፎ ማዕከል በማድረግ ይቀጥላል ብለዋል። 

በማጠቃለያው ላይ ሀሳብ የሰጡት ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ከምንጊዜውም በላይ እየተሻሻለ የመጣው የአመራር የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት በበጀት ዓመቱ ለተመዘገቡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች መሰረት ሆነዋል ብለዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ የፓርቲ እና መንግሥት ተቋማትን በማስተሳሰር ተግባር ተኮር ስምሪት መስጠት በመቻሉ እና በተለያዩ ጊዜያት ሀገራዊ እና ከተማ አቀፍ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በመሰጠታቸው በከተማዋ እየተመዘገቡ ላሉ አመርቂ ለውጦች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.