"ችግኞቻችንን እየተከልን በትዉልድ ላይ በጎ ሃሳብ ለመትከል የኮሙኒኬሽን መዋቅር ጉልህ ድርሻ አለዉ " ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ በ6ኛዉ ዙር የአረንጓዴ መርኃ ግብር “ የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ኪዳነ ምህረት ደን በመገኘት ለሁለተኛ ጊዜ የችግኝ ተከላ አካሒዷል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት የችግኝ ተከላዉን ያስጀመሩት የከተማው የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናትአለም መለሠ እንደተናገሩት ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ችግኝ ተከላ ስናካሄድ “ የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል ብቻ ሳይሆን በጎ ሃሳብን በከተማዉ ማህበረሰባችን ላይ በመትከል በጎ ሃሳብንና ልማትን ለትዉልድ የሚያስቀጥሉ ዜጎችን ማፍራት ነዉ ያሉት ኃላፊዋ ሀሳብን ለመሸጥ ደግሞ የኮሙኒኬሽን መዋቅር የበጎ ህሊናና አስተሳሰብ ፊት መሪ መሆኑን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የቢሮ ሃላፊዋ አክለዉም በዚህ ስራ በግንባር-ቀደምነት ለአስተበሰበሩ ለኮልፌ ቀራኒዮ አመራሮች፤ለቢሮ መዋቅር አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ልባዊ ምስጋናቸዉን አቅርበዉ ተግባሩ በልዩ ትጋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል፡:
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ ፍቃዱ በበኩላቸዉ በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ ሀሳብ አመጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ የደን መራቆትን የቀነሰ፤የብዝሀ ህይወት ጥበቃ ስራዎችን ያጠናከረ መሆኑን ገልፀው የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች የበለፀገች ሀገር ራዕይን ለማስፈን ትልቅ ሚና እያበረከተ ይገኛል ብለዋል. በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ የጥላ፤ የዉበትና የፍራፍሬ ችግኞች ሲተከሉ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ፤የአረንጓዴ ሽፋንን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ታሳቢ መደረጉ ተመላክቷል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሀ-ግብሩ ላይ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ፣በጎ የማህበረሰብ አንቂዎች ፣ወጣቶች፣የክፍለ ከተማውና የወረዳ አመራሮች፣የአካበቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.