"የሴቶች የፖለቲካው ተደራሽነት ለዲሞክራሲ ግንባታ የማይተካ ሚና አለው።" የአዲስ አበባ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ "ሁለተናዊ የሴቶች ዉሳኔ ሰጪነት ለዘላቂ ሠላም" በሚል መሪ ቃል በቀጣይ በሀገራችን የሚከበረዉን የሴቶች ቀን (ማርች 8) ታሳቢ በማድረግ ዉይይት አካሄደ።
የምክር ቤቱ የሴቶች ክንፍ ዋና ሰብሳቢ ወ/ት እመቤት ቢራራ በዓለም ለ113ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ በዓሉን ስናከብር እኛ ሴቶች በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ዙርያ ትርጉም ባለዉ መልኩ ምን ምን ስኬቶችን እንደተጎናፀፍን እና ምን አዬነት ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙን የምናይበትና በቀጣይ ይበልጥ ለመስራት መሠረት የምንጥልበት ነዉ ብለዋል።
ሰብሳቢዋ አክለዉም ያገኘነውን ህገመንግስታዊ መብት በመጠቀም ሀገራችን አሁን ካለችበት የሰላም እጦት ለማላቀቅ የእኛ የሴቶች በፖለቲካው ተደራሽነት ለዲሞክራሲ ግንባታ የማይተካ ሚና ስለሚኖረው እንደቀደምቶቹ ጀግኖች ሴቶቻችን ከፍተኛ ጥረት ልናደርግ ይገባልም ብለዋል።
የፌደራል የጋራ ም/ቤት የተፎካካሪዎች ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ቅድስት ግርማ በበኩላቸዉ በአዲስ አበባ የሴቶች ክንፍ ወደ ተግባር መግባቱን አዉስተዉ የዛሬዉ ዉይይት በዓሉን ከማክበር ባለፈ ተጨባጭ ለዉጦችን አጉልተን የምናይበት ለተሰሩ ስራዎች እዉቅና የምንሰጥበትና ለተግዳሮቻችን መፍትሔ የምናስቀምጥበት ነዉ ብለዋል።
በመጨረሻም ተሳታፊዎች ማርች 8 የሴቶችን ቀን ስናስብ የትናንት ስኬቶቻችንን የምናጠናክርበት በቀጣይ ስራችን ያሉብንን ተግዳሮቶች የምንፈታበት ነዉ ያሉ ሲሆን በክፍለ ከተማ እና በከተማ የተጀመረዉ መሠል ውይይት በቀጣይ በፌደራል ደረጃ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.