የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተለያየ ሪዮተ-ዓ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተለያየ ሪዮተ-ዓለም ልዩነት ቢኖረንም በሀገራዊ ጉዳይ የማንለያይ መሆናችንን የምናሳይበት ፣ ለሀገራችን አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት የጀመርናቸው መልካም ስራዎች አካል ነው - አቶ ሞገስ ባልቻ

ኢትዮጵያ የምትበለፅገው ሁሉንም አቅሞቿን ስታስተባብር ነው። እምቅ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶቿን በአግባቡ ጥቅም ላይ ካዋልን ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገራት ከደረሱበት ከፍታ የማትደርሰባት አንዳች ምክንያት የለም።

ፓርቲያችን በትብብር እና በፉክክር ለመስራት ግልፅ አቅጣጫ አስቀምጦ በተግባር እየተረጎመው የሚገኘው ሁሉም ታሪካዊ አሻራውን የሚያሳርፍበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በመረዳት ነው፡፡ ከመተባበር እንጅ ከመገፋፋት እንዲሁም ከመጠላለፉ አንዳች ትርፍ እንደማይገኝ ኢትዮጵያውያን ከመጣንበት መንገድ ጭምር ያረጋገጥነው እንጅ ለማለት ብቻ የምንለው አይደለም።

መቃወም ማለት ያለፈውን ትውልድ እንዲሁም ያሁኑን እየረገሙ እና እየተሳደቡ የራስን አሻራ ሳያሳርፉ ብኩን ሆኖ ማለፍ አይደለም :: 

በፖለቲካ ፕሮግራሞቻችን እንከራከራለን እንፎካከራለን ህዝባችን ደግሞ ዳኝነቱን ይሰጣል።

የህዝብ ዳኝነት ደግሞ ሪዮተ ዓለማችንን ብቻ ሳይሆን ለሀገር እና ለህዝብ ያለንን ውግንናም ግምት ውስጥ ያስገባል።

በየትኛውም ሀገር ጤነኛ ፖለቲካን የሚያራምድ ግለሰብም ይሁን ቡድን በሀገሩ ጉዳይ አይደራደርም። 

ለሀገር እና ለወገን መታገል ከንግግር ባሻገር በተፈጠሩት ምቹ ሁኔታዎች አሻራን ማሳረፍን ስለሚጨምር በተለይም 

የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት አንፀባራቂ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘውን የከተማችን ፈጣን ዕድገት በተለያዩ ጊዜያቶች በመጎብኘት ከሚሰጠው ገንቢ አስተያየት ባሻገር አረንጓዴ አሻራን በመሳሰሉ ሀገራዊ ጉዳዮች የሚያደርገው ተሳትፎም ይበል የሚያስብል መልካም ጅምር ነው።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እና ሌሎች የከተማ እና የክ/ከተማ እንዲሁም የወረዳ አመራሮች ከአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት አመራሮች ጋር "የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ቃል በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በሚገኘው ቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አከናውነዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በፕሮግራሙ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ብትሆንም በአግባቡ በመጠበቅ ለትውልድ ማሰተላለፍ ባለመቻሉ ተራቁታ መቆየቷን በመጠቆም ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ሀገራዊና ዓለም አቀፍዊ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ለመቅረፍ በህዝባችን በመተማመን በጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ባለፉት ስድስት ዓመታት ለዓለም ተሞክሮ የሚሆን ስኬት መመዝገቡን አስረድተዋል።

የከተማችን የአረንጓዴ ልማት ሽፋንም ከለውጡ በፊት ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ አሁን ላይ ከ 17 በመቶ ከፍ ማለቱን ያወሱት አቶ ሞገስ በዛሬው ዕለት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በከተማች በዚህ ክረምት 20 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ በቅርቡ የተጀመረው ንቅናቄ አካል መሆኑን አመላክተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተለያየ ሪዮተ - ዓለም ልዩነት ቢኖረንም በሀገራዊ ጉዳይ የማንለያይ መሆናችንን የምናሳይበት ፣ ለሀገራችን አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት የጀመርናቸው መልካም ስራዎች አካል ነው ያሉት ሀላፊው በተለይም የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ህዝቡ ችግኝ ከመትከል ባሻገር በአግባቡ በመንከባከብ የኢንዱስትሪ ፈርጥ የሆነውን ክ /ከተማ ከተፈጥሮ ጋር ለማስማማት የተጀማመረውን ሰፊ ስራ ማጠናከር እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ እንቆማለን ፣ እንደ ፖለቲካ ደግሞ እንደ አሰላለፋችን እንቆማለን ያሉት የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበባ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በበኩላቸው በክ/ከተማው ከአንድ ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት በአረንጓዴ የተሸፈነ መሆኑን ገልፀው በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች እየተሰራ ባለው የኮሪደር ልማትም የተበከሉ ወንዞች እየነፁ ፣ የተራቆቱ አካባቢዎችም አረንጓዴ እየለበሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ /ቤት ምክትል ሀላፊ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ ፣በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ /ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ይመር ከበደ ፣ የክ /ከተማ እና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎችም የተሳተፉ ሲሆን ለአቅመ ደካሞች የቤት ዕድሳት ማስጀመሪያ መርሀ -ግብርም ተከናውኗል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.