አዲስ አበባ በጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ አደባባይ ተሰየመላት!
በጀርመን የላይፕዚግ ከተማ በአዲስ አበባ የተሰየመ አደባባይ በሊፕዚግ እና በአዲስ አበባ መካከል የእህትማማች ከተማ አጋርነት 20ኛ ዓመት የማክበር ስነ-ስርዓት ላይ እ.ኤ.አ ነሀሴ 23 / 2024 ተመርቆ ተከፈተ።
በታሪካዊው የላይፕዚግ እምብርት ላይ የተካሄደው ስነ-ስርዓት ላይ የላይፕዚግ ከንቲባ ዩንግን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካዮች ፣ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካዮች ፣ የላይፕዚግ ባለስልጣናት እና በአካባቢው ያሉ የኢቲዮጵያ ማህበረሰብ አባላት የተሳተፉ ሲሆን፤ አደባባዩ በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን የላይፕዚግ ከንቲባ ዩንግ በአፅንኦት ገልፀዋል።
አዲስ አበባን ከንቲባን ወክለው የተገኙ የከንቲባ አማካሪ አቶ አሻግሬ ገብረወልድ የአደባባዩ መመረቅ ለሁለቱ ከተሞች እና ለሁለቱ ሀገራት ዘለቄታዊው ግንኙነት የላቀ ሚና እንደሚጫወት በመጠቆም በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአደባባዩ በአዲስ አበባ ከተማ መሰየም አጋርነትንና የጋራ ታሪክን ከመዘከር ባለፈ በቀጣይ ለሚደረጉ የሁለትዮሽ ትብብሮች መንገድ የሚከፍት መሆኑን አመልክተዋል።
ዝግጅቱ ሁለቱ ከተሞች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እና የጋራ ዕድገትን ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳየ ሲሆን ፣ አዲስ አበባም ይህን ጠቃሚ አጋርነት ለማስፋት ቁርጠኝነቷን አረጋግጣለች::
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.