በመዲናችን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት በልዩ ሁኔታ መሠጠት ተጀመረ፤
የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት በልዩ ሁኔታ ማስጀመሩን አስመልክቶ ዛሬ ለሚዲያ አካላት መግለጫ ሰጥቷል።
በዚሁ መሠረት የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባቱ እድሜያቸው 14 ዓመት ለሆናቸው ታዳጊ ሴቶች ብቻ የሚሰጥ ሲሆን ከየካቲት 25 እስከ 29 2016 ዓ.ም ባሉት ቀናት የሚሰጥ ይሆናል።
ዶ/ር ዮሐንስ በመግለጫቸው እንዳሉት በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የማህጸን በር ካንሰር በሽታን ከምንከላከልባቸው ስልቶች አንዱና ዋነኛው 14 ዓመት የሆናቸውን 90 ፐርሰንት የሚሆኑ ታዳጊ ሴቶችን በትምህርት ቤቶች እና ከትምህርት ቤቶች ውጪ በአቅራቢያቸው ክትባት እንዲያገኙ በማስቻል ነው ብለዋል።
ክትባቱ 31 ሺህ 485 ታዳጊ ሴቶችን ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዮሐንስ፣ 142 የክትባት ባለሙያዎች በትምህርት ቤቶች እና ከትምህርት ቤቶች ውጪ ለሚገኙ ታዳጊዎች ክትባቱን እንዲሰጡ የስራ ስምሪት እንደተሰጠ ተናግረዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሚገኙ 633 የመጀመሪያ ደረጃ እና 187 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 14 ዓመት የሆናቸው ታዳጊ ሴቶች ክትባቱ እንደሚሰጣቸው ኃላፊው አክለው ገልፀዋል።
በመጨረሻም የሚዲያ አካላት ለሕብረተሰቡ የክትባቱን አስፈላጊነት በሚመለከት ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶ/ር ዮሐንስ ክትባቱ በትምህርት ቤቶች፤ በጤና ጣቢያዎች እና በጊዚያዊ በተዘጋጁ የክትባት መስጫዎች የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.