የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በአዲስ አበባ በይፋ ተ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በአዲስ አበባ በይፋ ተጀመረ።

የአፍሪካ ከተሞች ፎረም የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ፣ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የአቻ አፍሪካ ሀገራትና የአለማቀፍ ተቋማት ሚኒስትሮች በተገኙበት የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ በአድዋ ድል መታሰቢያ ፓናፍሪካኒዝም አዳራሽ በይፋ ተጀምሯል።

በፎረሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም የፓን አፍሪካኒዝም መጸነሻ ስፍራ በሆነችው ኢትዮጵያ እንዲሁም በጥቁር ህዝቦች የነጻነት ታሪክ ውስጥ የማይፋቅ አሻራ ባሳረፈው የአድዋ ድል መታሰቢያ ማእከል በፓን አፍሪካኒዝም አዳራሽ መካሄዱ ልዩ እና ታሪካዊ ድምቀት እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡

ከንቲባዋ አክለውም ፈጣን እድገትና ለውጥ እየታየበት ባለው የግሎባላይዜሽን አለማቀፋዊ ሁኔታ በተለይ የአህጉራችን አፍሪካ ሀገራት ፈጣን የከተሞች እድገት ሊከሰት እንደሚችልና ይህን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው፣ የሁሉም ሃገራት ከንቲባዎች የአረንጓዴ ልማትን እና ለትውልድ የሚሻገሩ ምቹ የመኖርያ ከተሞችን በመገንባት ሂደት ውስጥ ሰርቶ ማሰራትን መርህ ያደረገ የበሰለ አመራር በመስጠት ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡  

የመዲናዋ እድገት መሰረቱ የህዝብን ፍላጎትና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች የልማት እቅድ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለከተማችን ነዋሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች መፍታት ብቻ ሳይሆን ከምንጩ ማድረቅ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ እና የቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራሞች፤ እንዲሁም የነገዋ የሴቶች ስብእና መገንቢያና የስራ ፈጠራ ማእከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ መሆናቸውንና አዲስ አበባ ወደ አለማቀፋዊ ተወዳዳሪ ከተማነት በፍጥነት እያደገች እንደምትገኝ ጭምር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አብራርተዋል፡፡

ፎረሙ ከነሃሴ 29 ለተከታታይ ሶስት ቀናት የአፍሪካ ከተሞችን ለዘላቂ ልማት መለወጥ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን በተለያዩ የከተሞች መሰረተ ልማት መስፋፋት ፣ ኢንቨስትመንት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.