ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ባለ አምስት ነጥብ የአዲስ አበባ ዲክላሬሽንን በማውጣት ተጠናቅቋል::
በፎረሙ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ የፎረሙ ጉባኤ ትርጉም ያላቸው ውይይቶች፣ ተሳትፎዎች እና የልምድ ልውውጦች በከተሞች መሪዎች የተካሄዱበት መሪዎች ተሻጋሪ እሳቤዎቻቸውን ለአፍሪካ የከተሞች ፎረም ዲክላሬሽን ግብዓትነት ያቀረቡበት ነው ብለዋል።
በፎረሙ የወጣው የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን ተራ ሰነድ ሳይሆን የአፍሪካን የወደፊት እድል የምንወስንበት ቃል ኪዳናችን ነው ብለውታል አቶ ጃንጥራር።
ከተሜነት ማህበራዊ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትን እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት እምቅ አቅም አለው ያሉት አቶ ጃንጥራር አባይ ይህን አቅም ለመጠቀም ግን ከቃላት ባለፈ የጋራ ግቦቻችንን ለማሳካት ተግባርን፣ ትብብርን እና ያልተቋረጠ ቁርጠኝነትን ይጠይቀናል ነው ያሉት።
የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የመሰረተ ልማቶች አለመሟላት ፣ ኢኮኖሚያዊ ኢ ፍትሃዊነትን የመሳሰሉ ተግዳሮቶች የምንጋራቸው ናቸው ያሉት አቶ ጃንጥራር በጋራ በመስራት ፣ ልምዶቻችንን በመለዋወጥ እና እርስ በራሳችን በመማማር እነዚህን ተግዳሮቶች መሻገር እንችላለን ነው ያሉት።
የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ፎረሙ የአፍሪካን የከተሜነት ምህዳር ለመለወጥ መሠረት ያስቀመጥንበት ነው ብለውታል።
በፎረሙ የከተሜነት ተለዋዋጭ ባህሪን ተረድተናል፣ ተግዳሮቶቻችን ላይ መክረናል፣ ለቀጣይ ጉዟችን የሚረዱ በፈጠራ ላይ የተመሠረቱ መፍትሄዎችንም በጋራ አስቀምጠናል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
የኢትዮጵያ መንግስት እና አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በማስተናገድ ስኬታማ እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋና ቀርቧል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.