የሪፎርም ቀንን ምክንያት በማድረግ በዲጂታላይዜሽን ስራዎች ሞዴል መሆን የቻሉ ተቋማት በዛሬው ዕለት በይፋ ተመረቁ።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥን ዉጤታማ እንዲሆን ለማስቻል በተለይም በሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ጽ/ቤት እና በስራና ክህሎት ጽ/ቤት የስራ አካባቢን ለተገልጋዮች ምቹ እና ዘመናዊ የማድረግ ስራ ሲሰራ የቆየ ሲሆን በዛሬዉ እለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ አብርሀም ታደሰ ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና እንዲሁም የክፍለ ከተማዉ ከፍተኛ አመራሮች እና የወረዳ አስተዳደሩ አመራሮች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል ።
በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ አብርሀም ታደሰ በመርሀ ግብሩ በመገኘት በከተማ አስተዳደሩ የሪፎርም ተግባራት አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን ጠቅሰዉ በአገልግሎት አሰጣጥ አሁንም ያልተሻገርናቸዉ ትኩረት የሚሹ ችግሮች በመኖራቸው በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በተቋማቱ የተመዘገቡ ስኬታማ ስራዎችን የበለጠ በማስፋት የህብረተሰቡ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎች መፍታት እንደሚገባ በማሳሰብ በ2017 በጀት ዓመትም የተሻለ አገልግሎት የሚሰጥበት እና ህዝብን በመልካም አገልግሎት የሚካስበት ዓመት እንዲሆንም ምኞታቸዉን ገልጸዋል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በበኩላቸው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ሪፎርም ተግባር እንደ ከተማ በተሳካ ሁኔታ መተግበሩን ገልጸዉ በክፍለ ከተማዉም የወረዳ 06 ሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ጽ/ቤት ሞዴል በመሆን እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም በሪፎርም ትግበራ እና የስራ ቦታን ምቹ በማድረግ ስራ ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእዉቅና እና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.