ሚዲያው እና የኮሙዩኒኬሽን አካላት በቅንጅት መሥራት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ፤
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ያዘጋጀው የጋዜጠኞች እና የኮሙዩኒኬሽን አመራር ክህሎት የሚያዳብር ሥልጠና በዓድዋ ድል መታሰቢያ የዓድዋ አዳራሽ ተሰጥቷል።
የሥልጠናው ዓላማ ጋዜጠኞች እና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች በተለይ የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ማስቻል ነው።
በሥልጠናው ላይ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሣሁን ጎንፋ እንዳሉት፣ ተቋሙ የጀመረውን የለውጥ ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል።
ኤኤምኤን አዲስ አበባን የተመለከቱ መረጃዎችን ለሕዝቡ በፍጥነት ለማድረስ ከኮሙዩኒኬሽን እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥልጠናውም የኤ.ኤም.ኤን ጋዜጠኞች እና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ለጋራ ግብ በቅንጅት የሚሠሩበትን መንገድ የማመቻቸት ዓላማም እንዳለው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ በበኩላቸው፣ ለሕዝብ የሚደርሱ መረጃዎች የኅብረተሰቡን ሕይወት የሚዳስሱ እና ችግሩን የሚቀርፉ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
ተቋማቱ ተቀናጅተው መሥራታቸው የተጀመረውን ከተማ አቀፍ ለውጥ ከማሳደግ ባለፈ ዓላማ መር የይዘት ሥራን በጋራ ለመሥራት ያግዛልም ብለዋል።
የሚዲያ ውድድሩ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የሚሠሯቸው የይዘት ሥራዎች አቀራረብ እና በይዘት ልቀው ሊገኙ እንደሚገባም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ሚኤሳ ኤለማ ደግሞ፣ የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን "ስትራቴጅክ ትብብር" በሚል ርዕስ በሰጡት ሥልጠና፣ መረጃዎችን በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል በመሆን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ለከተማዋ ልማት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በሥልጠናው የተሳተፉ ጋዜጠኞች እና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎችም ከሥልጠናው ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ክህሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ዘመኑን የሚመጥን የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ መሰል ሥልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፣ በተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን ለማዳበር የሚያስችሉ መድረኮችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.