ህዝበ ሙስሊሙ የተጀመሩ ልማቶችን በማፋጠን ሰላም...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ህዝበ ሙስሊሙ የተጀመሩ ልማቶችን በማፋጠን ሰላም፣ ልማትና አንድነትን እንዲያጠናክር ጥሪ ቀረበ

1499ኛው የነቢዩ ሙሀመድ(ሰዐወ) ልደት (የመውሊድ) በዓል በታላቁ አንዋር መስጂድ በድምቀት እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼይኸ አብዱልከሪም በድረዲን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መውሊድ ለሀገር ሰላም፣ ልማት እና አብሮነት የጎላ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ልማቶች መጠናቀቃቸውን እና እየተገነቡ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚደንቱ ህዝበ ሙስሊሙ ከምንጊዜውም በላይ ከመንግሥት ጎን በመቆም የተጀመሩ ልማቶችን በማፋጠን ሰላም፣ ልማትና አንድነትን እንዲያጠናክር ጥሩ አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ለነቢዩ ሙሀመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል እና ለመጅሊስ 50ኛ የምስረታ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ነቢዩ ሙሀመድ(ሰዐወ) በህይወት ዘመናቸው ያከናወኑትን መልካም ተግባራት በመውሰድ ራስን ለበጎ ተግባር በማዘጋጀት እና ለሠው ልጅ የሚበጅ መልካም ስራ በመስራት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሀገርና ከተማን በመገንባት አንዱ ለሌላው ጋሻና መከታ የመሆን ባህልን አጠናክሮ መቀጠል ይገባልም ብለዋል።

ነቢዩ ሙሀመድ(ሰዐወ) ለሰላም የነበራቸውን አስተምህሮ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው የመውሊድ በዓል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን እርስ በርሳችን በመደጋገፍ የጋራ ጉዳይ ላይ ካተኮርን ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ ናት ብለዋል።

የነቢዩ መወለድ ዋና ዓላማ ለሰው ልጆች እዝነትና ፍቅርን ማስተማር መሆኑን የገለፁት ዋና ጸሀፊው ህዝበ ሙስሊሙ ከሎሎች ወንድሞች ጋር በመሆን ለሀገር ልማት የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በሀገር ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር እያደረጉት ላለው አስተዋፅኦ ለማሕበራዊ ሚዲያ አንቂና የአባይ መብቶች የኢትዮጵያ ተሟጋች ለኡስታዝ ጀማል በሽር እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የአባይ ግድብ ተሟጋች መሀመድ አል አሩሲ ምስጋና አቅርበዋል።

በበዓሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የአባይ ግድብ ተሟጋች መሀመድ አል አሩሲ አማካኝነት የአባይ ወንዝ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን በተመለከተ በአረብኛ ቋንቋ መልዕክት ተላልፏል።

 


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.