አዲስ አበባ በፈረንጆቹ 2035 የአፍሪካ ቁልፍ ከተማ ትሆናለች
አዲስ አበባ በፈረንጆቹ 2035 የአፍሪካ ቁልፍ ከተማ እንደምትሆን የኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ያወጣው ሪፖርት አመላከተ፡፡
ተቋሙ “የአፍሪካ ከተሞች 2035” በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት አዲስ አበባን ጨምሮ መካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት ሊያድጉ እንደሚችሉ አስታውቋል።
እንደ ካይሮ፣ ሌጎስ እና ጆሃንስበርግ ያሉ የአፍሪካ ግዙፍ ከተሞች የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን እንደሚያስቀጥሉ ሲጠበቅ እንደ አዲስ አበባ ያሉ መካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉ ከተሞች ደግሞ ከፍተኛ ፍጥነት ያለውን ዕድገት እንደሚያስመዘግቡ ትንበያው አመላክቷል፡፡
አዲስ አበባን ተከትለው ከፍተኛ ዕድገት እንደሚያስመዘግቡ ከተገመቱት ከተሞች መካከል ብራዛቪል፣ ዳሬሰላም እና ሉዋንዳ ይገኙበታል።
ዕድገቱ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን፣ የከተሞች መስፋፋት እና በአቅራቢያ ያሉ የትላልቅ ከተሞች መፈጠር አንደሚያካትት ሪፖርቱ ያመላክታል።
ከአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ በማስመዝገብ አንዷ ሆና እውቅና ያገኘችው አዲስ አበባ እስከ ፈረንጆቹ 2035 ድረስ በዓመት ባለ ሁለት አሃዝ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት (ጂዲፒ) እንደምታስመዘግብም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በአንፃሩ እንደ ናይሮቢ እና አቡጃ ያሉ ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከ6 በመቶ እስከ 8 በመቶ የዕድገት ምጣኔ እንደሚኖራቸውም ሪፖርቱ ይጠቅሳል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.