የመስቀል መደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ለሚያስተባብሩ የከተማው ወጣቶች የስራ ስምሪት ተሰጠ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም ፀጥታ ቢሮ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በመሆን የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ለሚያስተባብሩ 310ሺህ ለሚሆኑ የከተማው ወጣቶች የስራ ስምሪት ሰጥተዋል።
በዓላቱ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ የከተማው ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው በተሰጣቸው ስምሪት መሰረት እንዲሰሩ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ም/ቢሮ ሀላፊ ተስፋዬ ደንድር አሳስበዋል።
በአላቱ የሚከበሩባቸው ቦታዎች እንዲሁም የአከባቢያቸውን ብሎም የከተማቸውን ሰላም ነቅተው እንዲጠብቁ የተናገሩት አቶ ተስፋዬ በበዓላቱ እንዳይያዙ የተከለከሉ ነገሮችን እና በኮሪደር ልማት የተሰሩ የልማት ስራዎችን እንዲቆጣጠሩ አሳስበዋል።
ከከተማው ወጣቶች እና የስፖርት ቤተሰቦች ጋር ከክፍለ ከተማ እስከ ብሎክ በመስቀል እና በኢሬቻ በዓላት አከባበር ዙሪያ ተከታታይነት ያለው ውይይት መደረጉን እና የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ያስታወሱት አቶ ዳዊት ትርፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ም/ቢሮ ሀላፊ ዛሬ በከተማ ደረጃ የማጠቃለያ ውይይት እና የስራ ስምሪት እንደተሰጠ ተናግረዋል።
ወጣቱ ትውልድ ከአባቶቹ የተቀበላቸውን ባህሎች እና ታሪኮች በሚገባ ተረድቶ እና እሴቶቻቸውን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራ እንዳለበትም አቶ ዳዊት አሳስበዋል።
በከተማ ደረጃ በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ ጥምር የሰላም እና የፀጥታ ግብረ ሀይል መቆቆሙን እና ወደ ስራ መግባቱን የተናገሩት ረዳት ኮማንደር አይናለም በየነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማህበረሰብ ፖሊስ አገልግሎት ሀላፊ ወጣቶች ከተቋቋመው ግብረ ሀይል ጋር በመቀናጀት እንዲሰሩ ተናግረዋል፡፡
በማጠቃለያ ውይይቱ እና በስራ ስምሪቱ ላይ የተገኙ የከተማው ወጣቶች የመሰቀል እና የኢሬቻ በአላት በሰላም እንዲከበሩ በተሰጣቸው የስራ ስምሪት መሰረት ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በዓላቱን ለማክበር ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ የዕንግዳ አቀባበል ስነ ምግባር እንግዶችን ተቀብለው በማሰተናገድ እንደሚሸኙ ወጣቶቹ የተናገሩ ሲሆን በዓላቱ ካለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል ።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.